ቀጥታ፡

አባቶቻችን ለኢትዮጵያ ልዕልና የፈጸሙት ገድል ለዛሬው ትውልድ ትልቅ ትምህርት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፡- አባቶቻችን ለኢትዮጵያ ልዕልና የፈጸሙት ገድል ለዛሬው ትውልድ ትልቅ ትምህርት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን ከትናንት በስቲያ አካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም፤ አባቶቻችን ለኢትዮጵያ ልዕልና የፈጸሙት ገድል ለዛሬው ትውልድ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ሀገርን እንደ ቤት በመመሰል በሰጡት ማብራሪያ፤ የቤቱን ቀለም ከመቀየር ይልቅ የቤት ምሰሶ የሆነውን ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ አካላት መኖራቸው ትልቅ ስጋት መሆኑን ተናግረዋል።

የፖለቲካ ስብዕና ልኬት በሥርዓት እንጂ በሀገር ህልውና ላይ በሚመጣ አደጋ መሆን እንደሌለበትም አስገንዝበዋል።

ምሰሶው በሌለበት ስለ ግድግዳው ቀለም መጨቃጨቅ ትርጉም የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲቀየሩ መጠየቅ መብት ቢሆንም በኢትዮጵያ ህልውና ላይ መደራደር ግን ትክክል እንዳልሆነ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የገጠሟት ጠላቶች ፍላጎት የሀገሪቱን ምሰሶ ማፍረስ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያን ምሰሶ ከሚያፈርሱ አካላት ጋር መስራት አደጋው የከፋ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለዚህም ታሪካችን ጥሩ አስተማሪ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አባቶቻችን ለኢትዮጵያ ልዕልና የፈጸሙት ገድል ለዛሬው ትውልድ ትልቅ ትምህርት ነው ብለዋል።

ለአብነትም የሀገር ሉዓላዊነት ሲደፈር ጸቤ ከሀገሬ ጋር አይደለም በማለት ለኢትዮጵያ ህልውና መስዋዕት የሆኑ ጀግና አርበኞችን አስታውሰዋል።

በዚህ መነሻነትም የዛሬው ትውልድ ቀደምት ጀግኖች የተለሙትን መንገድ በመከተል ሀገርን ማስቀደም ዋነኛ ምርጫው ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድ በኢትዮጵያ የጋራ ምሰሶ ላይ ጽኑ አቋም በመያዝ ለሀገር ክብርና ልዕልና መታመን እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል።

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም