ቀጥታ፡

በሊጉ ነገሌ አርሲ ከመቀሌ 70 እንደርታ ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከነማ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይጠበቃሉ  

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ነገሌ አርሲ ከመቀሌ 70 እንደርታ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ነገሌ አርሲ በሊጉ ካደረጋቸው 18 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኝ ጊዜ ሲያሸንፍ በአራቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በአምስት ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ 20 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን አስተናግዷል። 

አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በ32 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው መቀሌ 70 በውድድር ዓመቱ 18 ጨዋታዎችን አከናውኖ በሶስቱ ድል ሲቀናው ስድስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 13 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 21 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

መቀሌ 70 እንደርታ በ18 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ነገሌ አርሲ ካሸነፈ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ የጣለው መቀሌ 70 እንደርታ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

በሌላኛው መርሐ- ግብር  ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

ኢትዮጵያ መድን እስከ አሁን በሊጉ 18 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን አራት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ተሸንፏል። በሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 

በ18ቱ ጨዋታዎች ላይ 12 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 15 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ19 ነጥብ 16ተኛ ደረጃን ይዟል። 

ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ካከናወናቸው 17 ጨዋታዎች መካከል ስምንት ጊዜ ድል ሲቀናው የተሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 14 ግቦችን ሲያስቆጥር 7 ጎሎች ተቆጥረውበታል። 

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ፋሲል ከነማ በ32 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ፋሲል በዘንድሮው የውድድር ዓመት ዝቅተኛ የግብ መጠን እና ሽንፈት ያስተናገደ ቡድን ነው። 

ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል የራቀው የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና እንዲርቅ ያደርገዋል። 

ፋሲል ከነማ በሊጉ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ23 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በ16 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። 

ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶስት ነጥብ የመጀመሪያውን ዙር በድል ለማጠናቀቅ ያስችለዋል። 

በ18ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ያስተናገደው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ባህርዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ በርካታ የአቻ ውጤቶችን (11) ያስመዘገበው ባህርዳር ከተማ በ23 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ20 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። 

ባለፉት አራት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ባህርዳር ከተማ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ይጫወታል። 

በ18ኛ ሳምንት በነገሌ አርሲ የ2 ለ 0 ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም