ቀጥታ፡

‎በአማራ ክልል የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ባህርዳር ፤ጥር 27/2018(ኢዜአ)፡- ‎በአማራ ክልል የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት ላይ ያተኮረ ክልላዊ ፎረም ዛሬ በባህርዳር ተመስርቷል ።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊና የፎረሙ ሰብሳቢ ብርቱካን ሲሳይ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣በክልሉ የሴቶችን አቅም ለማጎልበትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።


 

የፎረሙ ዋና ዓላማ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን አንዲያጠናክሩ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

ሴቶች በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የፎረሙ መመስረት የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመልክተዋል።

‎የፎረሙ አባል ተቋማት በመደበኛ ስራዎቻቸው የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራትና ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

‎ሴቶች ወደ ስራ ለመግባት በሚያደርጉት ጥረት የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ ችግር ለመፍታት የፋይናንስ ምንጭን ማስፋት ላይ የተቋማት ርብርብ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

‎የክልሉ ሥራና ሥልጠና ቢሮ ኃላፊና የፎረሙ ምክትል ሰብሳቢ ስቡህ ገበያው (ዶ/ር) በበኩላቸው ሴቶችን በሚፈልጉት ሙያ በማሰልጠን፣ በማደራጀትና ወደ ስራ በማስገባት ረገድ በሚደረገው ጥረት የመሬትና የብድር አቅርቦት እጥረት ዋነኛ ችግር መሆኑን አንስተዋል።

የፎረሙ መመስረት እንደዚህ አይነት ችግሮችን በተቀናጀ አግባብ በመፍታት የሴቶችን ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ያስችላል ብለዋል።


 

የፎረሙ መቋቋም ሴቶች በግብርናው ዘርፍ ተሰማርተው ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት ዕድል ይፈጥራል ያሉት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊና ‎የፎረሙ አባል ደረጀ ማንደፍሮ ናቸው።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ በበኩላቸው፣ሴቶችን የገጠር መሬት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ፎረሙ ተግባሩን የበለጠ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

‎በፎረሙ መመስረቻ መድረክ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ከክልል እስከ ዞን የሚገኙ ሴት አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም