በምስራቅ ቦረና ዞን በዘንድሮው ዓመት ከ178 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን በዘንድሮው ዓመት ከ178 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበልግ ይለማል
ነገሌ ቦረና፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን በዘንድሮ የበልግ አዝመራ ከ178 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ዝናብ አጠር ዞኖች ከሆኑት አንዱ የምስራቅ ቦረና ዞን ነው።
ዞኑ አርብቶ አደር ማህበረሰብ የሚበዛው ቢሆንም የክልሉ መንግስት የተለያዩ ኢንሼቲቮችን ቀርጾ ማሕበረሰቡ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በሌሎች የእርሻ ልማት በመሳተፍ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ እያደረገ ነው።
በተለይም አካባቢው የበልግ አብቃይ እንደመሆኑ ያሉትን የውሃ አማራጮች በመጠቀም ምርትና ምርታማቱን ለማሳደግ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ቦነያ ሁቃ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ፤በዞኑ በአብዛኛው ቆላማ ወረዳዎች የዝናብ እጥረት በማጋጠሙ ባለፈው የመኸር ወቅት የሚጠበቀው ምርት ለማግኝት አልተቻለም።
ይህንን ለማካካስ በዘንድሮው የበልግ ወቅት 178 ሺህ 713 ሄክታር መሬት ለማልማት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ 48 ሺህ 773 ሄክታር መሬት ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
ዞኑ ከበልግ ወቅት የእርሻ ስራ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ማቀዱን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት የማሳ ዝግጅት ስራውን የሚያሳልጡ በርካታ ትራክተሮች ወደ ዞኑ የገቡ ሲሆን፤ ከ78 ሺህ በላይ ከፊል አርብቶ አደሮችም በዚሁ ስራ ላይ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በልማቱ ከተሳተፉት ከፊል አርሶ አደሮች መካከል በዞኑ ሊበን ወረዳ የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዲኑር መሀመድ እንዳሉት፤ በበልግ አዝመራው የተሻለ ምርት ለማግኘት እንዲቻል የማሳ ዝግጅት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ባለፈው መኸር የምርት እጥረት አጋጥሞ የነበረ ቢሆንም በዘንድሮው አመት የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እየተጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በሊበን ወረዳ የሲሚንቶ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሁሴን አብዱላሂ በበኩሉ በበልግ አዝመራው ስንዴና ጤፍ ለማልማት የማሳ ዝግጅት መጀመሩን ይናገራል።
የሊበን ወረዳ ቆላና ዝናብ አጠር ቢሆንም በበልጉ አዝመራ የተሻሻለ የግብርና አሰራርና የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ጥሩ ምርት የመሰብሰብ ልምድ እንዳለው ነው የሚገልፀው።