ቀጥታ፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ አካታች፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የድርሻችንን እንወጣለን-ወጣት አደረጃጀቶች

ጂንካ፤ጥር 27/2018 (ኢዜአ) :- በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ  ምርጫው ነፃ፣ አካታች፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣት አደረጃጀት ተወካዮች ገለፁ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን የ6 ወራት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በጂንካ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አማኑኤል ሳሙኤል በወቅቱ እንደገለፀው ከለውጡ ወዲህ የክልሉ ወጣቶች በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ከዳር ተመልካችነት ወደ መሪ ተዋናይነት ተሸጋግረዋል።

የክልሉ ወጣቶች ገዢ ትርክትን በማስረፅ ወጥ የሆነ ሀገራዊ እይታ እና አስተሳሰብ እንዲጎለብት ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ነው የገለጸው።

የክልሉ ወጣቶች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፍፁም ሰላማዊ፣ ነፃ፣ አካታችና ፍትሀዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቁሟል።

በክልሉ የወጣቶች ተወካዮችን በማስተባበር፣ግንዛቤ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


 

የክልሉ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ሰላማዊት ኃይሉ በበኩሏ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነገዋን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረግ ርብርብ  አካል እንደሆነ አንስታለች ።

ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ግንዛቤ በመስጠት የክልሉ ወጣቶች በመራጭነት፣ በተመራጭነት እና በአስተባባሪነት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እየሰራን ነው ብላለች።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊ፣ በህዝብ ዘንድ ተአማኒና ቅቡልነት ያለው እንዲሆን ምክር ቤቱ የድርሻውን ይወጣል ያለው ደግሞ የክልሉ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወጣት ቲቶ ሀኩት ነው።


 

የክልሉ ወጣቶች የምርጫውን ዴሞክራሲያዊነት  በማስጠበቅ  ክልሉ የሰላም ተምሳሌት መሆኑንም በተግባር ማረጋገጥ ይገባናል ሲል ነው የተናገረው።

በምክክር መድረኩ ላይም የክልሉ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎችና የወጣት አደረጃጀት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም