በክልሉ የትምህርት ተሳትፎና ጥራትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ድርሻ የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ተሳትፎና ጥራትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ድርሻ የጎላ ነው
ቦንጋ፣ ጥር 27 /2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የትምህርት ተሳትፎና ጥራትን ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ድርሻ የጎላ እንደነበረ ተገለጸ።
በክልላዊ የትምህርት ልማት ተግባራት የሚዲያ ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት በተርጫ ከተማ ተካሄዷል።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ አለሙ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተዘረጋው ቅንጅታዊ ተግባራት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ድርሻ ከፍተኛ ነው።
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ተቋማቱ ተማሪዎችን በስነ-ምግባር ግንባታና ኩረጃን የሚጸየፍ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ተከታታይ አጀንዳ በመቅረጽ መስራታቸውን አስረድተዋል።
የትምህርት ተሳትፎና ጥራትን ለማረጋገጥ የባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲጠናከር ተከታታይ ዘገባዎች ማቅረባቸውንም አንስተዋል።
በመድረኩ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደስታ ገነሜ (ዶ/ር)፣ ለሀገር ግንባታ ስራ ስኬታማነት የትምህርቱ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
በትምህርት ዘርፉ የገጠሙ ስብራቶችን ለመጠገንም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
ለዚህም በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በገንዘብ፣ በጉልበትና በዓይነት አንድ ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ለትምህርት ልማት እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና የትምህርት ቤቶች እድሳት ጥገና እንዲሁም ሞዴል ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶችን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ገልፀዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅም የትምህርት ቤት ምገባና የመምህራን አቅም ግንባታ በቅንጅት መሰራቱን አንስተዋል።
በሂደቱም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ግንዛቤ በመፍጠር የህብረተሰቡንና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲያድግ ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን ጠቅሰዋል።
በመድረኩ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መብራቱ መርክኔ የትምህርት ልማት ለሀገር ግንባታ መሠረት መሆኑን አንስተዋል።
ለተግባራዊነቱም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ትርክትን በመገንባትና የትምህርት ጥራትን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ መስራቱን ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የፎረሙ ተሳታፊዎች ትምህርት ላይ መስራት ሀገርን ማስቀጠልና ትውልድን መገንባት በመሆኑ የድርሻቸውን መወጣታችውን አንስተዋል።
በቀጣይም በየደረጃው ከሚገኙ የዘርፉ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ያሉትን ተግባራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።