በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ውጤታማ የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ውጤታማ የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ተከናውነዋል
ሐዋሳ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ) :- በሲዳማ ክልል በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት ውጤታማ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አብርሀም ማርሻሎ አስታወቁ።
በክልሉ የመንግስትና የፓርቲ የግማሽ በጀት አመት አፈጻጸም ግምገማና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሐዋሳ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አብርሀም ማርሻሎ መድረኩን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ጊዜ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አርሶ-አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን የዶሮና የወተት ላሞችን በማቅረብና በማዳቀል አርሶ አደሩ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዲችል መደረጉን ጠቁመዋል።
የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት ጥረት መደረጉን ጠቅሰው፣ በመንገድ፣ በመጠጥ ውሃ አቅርቦትና በሌሎችም አበረታች ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።
በክልሉ በሁሉም ከተሞችና በገጠር እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ለስራ፣ ለኑሮና ለመዝናኛ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውንም ነው ያብራሩት።
ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ከሐዋሳ በተጨማሪ በሌሎች ከተሞች ለማስጀመር ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል።
ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፈትሃዊና ነጻ እንዲሆንም እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዛሬን ጨምሮ ለቀጣዮቹ ሶስት ቀናት በሚካሄደው የግምገማ መድረክ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የካቢኔ አባላት፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የፓርቲ ጽህፈት ቤት አመራሮች እየተሳተፉ ነው።