የህዝብን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ የወጡ አዋጆችን በቁርጠኝነት መተግበር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ የወጡ አዋጆችን በቁርጠኝነት መተግበር ይገባል
ድሬደዋ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦ የህዝብን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ የወጡ አዋጆችን በቁርጠኝነት መተግበር እንደሚገባ የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ አብዲ ሙክታር አስገነዘቡ።
ለሁለት ቀናት የተካሄደው የድሬደዋ አስተዳደር ምክርቤት 3ኛ የስራ ዘመን 5ኛ አመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችን በማፅደቅ ዛሬ ተጠናቋል።
ለሁለት ቀናት የተካሄደው ጉባኤው የአስፈፃሚውንና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የግማሽ በጀት አመት የስራ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
ከፀደቁ ረቂቅ አዋጆች መካከል የድሬደዋ አስተዳደር የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር፣ የአስፈፃሚና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋምና ተግባርና ኃላፊነታቸውን ለመወሰን የወጡት አዋጆች ተጠቃሽ ናቸው።
በተጨማሪም ከኃላፊነት የሚሰናበቱ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላት፣ የፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶችና ዳኞች የሚያገኟቸውን መብቶችና ጥቅሞች ለመወሰን የወጣን አዋጅ ለማሻሻል በተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ አፅድቋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክርቤት አፈጉባኤ አቶ አብዲ ሙክታር በወቅቱ፤ የፀደቁት ረቂቅ አዋጆች የህዝብን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተናበበ መንገድ ለመመለስ መደላድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።
በተለይም ድሬደዋን ስማርት ከተማ ለማድረግና በየደረጃው የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተደራሽና ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትን ይበልጥ ለማሳደግ ያስችላሉ ብለዋል።
እነዚህን አዋጆች በቅንጅት በመተግበር የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መትጋት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
ለዚህም ምክርቤቱ የሚያደርገውን ክትትልና ድጋፍ እንደሚያጠናክር በመግለፅ።