የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ለግሉ ዘርፍ ምቹ መደላድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ለግሉ ዘርፍ ምቹ መደላድል ፈጥሯል
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ለግሉ ዘርፍ ምቹ መደላድል መፍጠሩን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
15ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት "የኢትዮጵያን ይግዙ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ መካሄድ ጀምሯል።
በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ይህ የንግድ ትርኢት ከዛሬ ጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ ምቹ መደላድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በዚህም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በሚከናውኑ ተግባራት የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ድርሻ በከፍተኛ ፍጥነት ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት የሀገር ውስጥ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የገበያና የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
በቀጣይም የግሉ ዘርፍ በንግድና ኢንቨስትመንት ያለውን ተሳትፎ ለማሻሻል የሚደረጉ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ በበኩላቸው፤ የሀገሪቷን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ምክር ቤቱ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ የጎላ ተሳትፎ እንዲኖረው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከማድረጉም ባለፈ፣ የሀገሪቱን የንግድ እንቅስቃሴ በማነቃቃትና አዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ቀነኒሳ ለሚ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በንግድ ትርኢቱ ላይ ከ300 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ድርጅቶች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህም መካከል ከ20 በላይ ከሚሆኑ ሀገራት የመጡ 50 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ይገኙበታል።
ዝግጅቱ ምርትን ከማስተዋወቅ ባለፈ በተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሳለጥ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።