በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል
ጂንካ፤ጥር 27/2018(ኢዜአ) :- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመጀመሪያው ግማሽ በጀት ዓመት ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ የበጎ ፈቃድ ስራ መከናወኑን የክልሉ ወጣቶችና በጎ ፍቃድ አገልግሎት ኮሚሽን አስታወቀ ።
የኮሚሽኑ 2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም በጂንካ ከተማ እየተገመገመ ነው።
ኮሚሽነሩ ማርቆስ ማቲዎስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባለፉት ስድስት ወራት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአረጋውያንን ቤት የማደስ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የትራፊክ ደህንነት፣ የአካባቢ ውበትና ፅዳት፣ ትምህርት እና የደም ልገሳ ተግባራት ተከናውነዋል።
በዚህም ወደ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በበጎ ፈቃድ ስራው ከ 2 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የመንግስት ሃብትን ማዳን መቻሉንም ገልፀዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአዕምሮ እርካታና ትስስርን የሚያጠናክር በመሆኑም በበጋው ወቅትም ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው ያረጋገጡት።
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው በዞኑ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል።
የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አንስተዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች ለወገናቸው አለኝታነታቸውን የገለፁበትና የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ልምዳቸውን ይበልጥ ያጠናከሩበት እንደሆነም አንስተዋል።
የዞኑ አስተዳደር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ የክልሉ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎች፣ የወጣት አደረጃጀት ኃላፊዎችና የወጣት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።