ቀጥታ፡

የትራፊክ አደጋ የሚያስከትለውን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል

ሰመራ፣ጥር 27/2018(ኢዜአ):- የትራፊክ አደጋ የሚያስከትለውን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ቅንጅታዊ አሰራርን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱ የመንገድ ደህንነት አጠቃቀምን በተመለከተ በአፋር ክልል የባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።



 

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ትዕግስቱ አምሳሉ የመንገድ ደህንነትን ማረጋገጥ በትራፊክ አደጋ የሚደርሰውን ጫና ይቀንሳል ብለዋል።

የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ላይ አሽከርካሪዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ተቆጣጣሪዎች በትኩረት እየሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በትራፊክ አደጋ ምክንያት የበርካታ ዜጎች ህይወት የሚያልፍ ሲሆን ተደጋጋሚ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመትም እያጋጠመ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም በሀገርና ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያስከትል መሆኑን ጠቅሰው፣ ጫናውን ለመቀነስ ቅንጅታዊ አሰራርን የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

አፋር የገቢና ወጪ ንግዱ ኮሪደር እንደመሆኗ በመንገድ ደህንነት አጠቃቀም ላይ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

የአፋር ክልል የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሁሴን ቦልኮ በበኩላቸው፣የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ የወጣውን ደንብ በአግባቡ ተረድቶ ማስፈጸም የባለድርሻ አካላት ሃላፊነት ነው ብለዋል።


 

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በትራፊክ አደጋ ይደርስ የነበረው ጉዳት መቀነሱን ጠቅሰው፣ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አሽከርካሪዎችን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ በክልሉ የሚገኙ የመንገድ ተቆጣጣሪዎች፣ የትራፊክ ፖሊሶች፣ የጤና እና ትራንስፖርት ዘርፍ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም