ቀጥታ፡

የዕዳ ጫናን ለመቀነስ እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሄ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ለመቀነስ እየተወሰዱ ያሉ የመፍትሄ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ፕሮጀክት ለምዕራፍ ሁለት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ አስረጂ የውይይት መድረክ አካሂዷል።


 

በውይይት መድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የብድር ሥምምነቱን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው የብድር ሥምምነቱ ለጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁስ በማሟላትና ባለሙያዎችን በማሰልጠን ህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

ለዚህም 30 ሚሊዮን ዶላር ኮንሴሽናል ብድር ከደቡብ ኮሪያ ኢምፖርት ኤክስፖርት ባንክ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው፥ ብድሩ በ40 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ 0 ነጥብ 01 በመቶ ወለድ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የዕዳ ጫናን ለመቀነስ ተግባራዊ የተደረጉ የመፍትሄ እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር ምንም ዓይነት የኮሜርሺያል ብድር አልወሰድንም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከአበዳሪ ሀገራት ጋር በመደራደር የዕዳ ሽግሽግ እንዲደረግ ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

ጥቅል ሀገራዊ ምርትና የወጪ ንግድ እያደገ መምጣቱን ገልጸው ፤ ይህም የዕዳ ጫናን መቀነስን ጨምሮ ጤናማ የፋይናንስ ስትራቴጂ ተግባራዊ በመደረጉ የመጣ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነትም በረጅም ጊዜ የሚመለስ እና ዝቅተኛ ወለድ ያለው መሆኑ ከአጠቃላይ የብድር ስትራቴጂ አኳያ ተፈላጊ ነው ብለዋል።


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላቸው፤ የዕዳ ጫናን ለመቀነስ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የሚበረታቱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ ሁለት ማስፈጸሚያ የሚውለው የብድር ስምምነት፥ የጤና ተቋማትን የህክምና ግበዓት እጥረት ለመፍታት አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

አዋጁ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም