የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመን የተተገበሩ ሪፎርሞች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመን የተተገበሩ ሪፎርሞች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማዘመንና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እየተተገበሩ የሚገኙ የሪፎርም እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው በመንግሥት የ6 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማዘመንና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት መጠነ ሰፊ ሪፎርም በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በባንኮች እርስ በእርሳቸው የገንዘብና የዶላር ግብይት እንዲፈጽሙ በማድረግ፥ ባለፈው ስድስት ወር ከግማሽ ትሪሊየን ብር ያላነሰ ገንዘብ እርስ በእርስ መገበያየታቸውን ገልጸዋል።
ይህም ትልቅ የገንዘብ ምንጭ ማስፊያ መንገድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ምክንያት በስድስት ወራት የገንዝብ አቅርቦቱ ከ10 በመቶ በላይ ቁጠባ ደግሞ ከ44 በመቶ በላይ ማደጉን ነው የተናገሩት፡፡
የተሰበሰበ ብድርም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 68 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰው አዲስ የቀረበው የብድር መጠንም በ123 በመቶ ማደጉን አብራርተዋል፡፡
አጠቃላይ የቀረበው ብድር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 123 በመቶ የጨመረ ሲሆን፥ ከቀረበው ውስጥ 90 በመቶው ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ መሆኑን ገልጸው በዘርፉ ትልቅ እመርታ እየመጣ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች መከፈቱ ካፒታል እና ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን በማንሳት፥ ለዘርፉና ለአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ነው ያስረዱት።
የሀገር ውስጥ ባንኮች ለኢኮኖሚው ያላቸው ድርሻ ከ5 እስከ 7 በመቶ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ውድድርን ለመፍጠርና ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የውጭ ባንኮች መግባት አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።
በዚህ ሂደት የሀገር ውስጥ ባንኮችን ጥቅም ለመጠበቅ የባለቤትነት ድርሻ ገደብ መቀመጡን ገልጸው፤ በአጠቃላይ በዘርፉ የውጭ ባለሀብቶች ድርሻ ከ49 በመቶ እንደማይበልጥ አስረድተዋል።
ይህ ሪፎርም የሀገሪቱን የፋይናንስ አቅም በማጠናከር ለዜጎችና ለንግዱ ማህበረሰብ የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው አመላክተዋል።