የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን የዕዳ ጫና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን የዕዳ ጫና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን የዕዳ ጫና በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው በመንግሥት የ6 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የለውጡ መንግሥት በዕዳ ቅነሳና አስተዳደር ሥራ ሊመሰገን የሚገባው ሥራ መሥራቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት በከባድ የዕዳ ጫና ውስጥ እንደነበረች ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም ቀደም ሲል ይወሰድ የነበረው የንግድ ብድር ለሀገሪቱ ትልቅ ፈተና ሆኖ እንደነበር ጠቁመዋል።
ይህ ዓይነቱ ብድር የሀገሪቱን የፋይናንስ አቅም ያዳከመና አበዳሪዎች ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲጠራጠሩ ያደረገ መሆኑንም አስታውሰዋል።
የሌብነት መስፋፋት እና የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ድክመት ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦት እንደነበርም አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ የዕዳ ጫናዋን ከመቀነስ ባለፈ አንድም የንግድ ብድር አለመውሰዷን ጠቁመዋል።
ይህ እርምጃ ምስጋና የሚገባው ጠንካራ የፖሊሲ አቅጣጫ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ቀድሞ የተወሰዱ የንግድ ብድሮችን ወደ መደበኛ ብድር ለመቀየር የተደረጉ ድርድሮች ስኬታማ መሆናቸውን አንስተዋል።