በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች ለዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች ለዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችና በሁሉም መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች ለዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ በትናንትናው ዕለት ማካሄዱ ይታዎቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሥራና ክህሎት ልማት ማብራሪያቸው÷ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በሀገር ውስጥ በተፈጠረው መጠነ ሰፊ የሥራ ዕድል ውስጥ የኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችና በሁሉም መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የከተማና ገጠር የኮሪደር፣ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና፣ ማዕድን፣ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና የአዳዲስ ነፃ የንግድ ቀጣናዎች ስኬት ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ድርሻ መያዛቸውን አስረድተዋል።
በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪትም በግማሽ ዓመቱ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ አንስተዋል።
በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት የሚላኩ ዜጎችም የቋንቋና የሙያ ክህሎት ስልጠና በብቃት መመዘኛ አልፈው በሀገራቱ ምቹ የሥራ ቆይታ እንዲኖራቸው እያስቻለ መሆኑን አብራርተዋል።
ከእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎች ሀገራት ጋር የተወሰዱ የሁለትዮሽ ስምምነት ኢትዮጵዊያን መብትና ጥቅማቸው ተጠብቆ የሥራ ዕድል የሚያገኙበት ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር በሥራ ስምሪት መስክ የምትፈራረማቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶችም የዜጎችን ሕገወጥ ስደት በመቀነስ ለሚደርስባቸው እንግልት መፍትሔ እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።