በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 709 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 709 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ ተችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ 709 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ በትናንትናው ዕለት አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሀገራዊ የገቢና ወጪ ዘርፍ ማብራሪያቸው÷ የኢትዮጵያን የገቢ አቅም ለማሳደግ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት 1 ነጥብ 2 ትርሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን አስታውሰዋል።
በዕቅዱ መነሻነትም ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 709 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።
በዚህ ወር ባለፉት ሃያ አምስት ቀናት ውስጥም 85 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ እንደተቻለ አስረድተዋል።
የበጀት ዓመቱ የሰባት ወራት ገቢን የመሰብሰብ አቅም እስከ 815 ቢሊየን ብር ሊደርስ እንደሚችል አብራርተዋል።
በቀጣይም ገቢ የመሰብሰብ አቅምን በማሻሻል በፌደራል 1 ነጥብ 5 ትርሊየን ብር በክልሎች 1 ትርሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ድምር 2 ነጥብ 5 ትርሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ ከተቻለም ከሀገር ውስጥ ጥቅል ዕድገት 9 በመቶ አካባቢ መድረስ እንደሚቻል ተናግረዋል።
በተጨማሪም የገቢ አቅምን በማሳደግ በተመጣጠነ የወጪ ሥርዓት የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞ ለማሳለጥ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል።