ቀጥታ፡

ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት የሚደረገው በዘርፉ ተወዳዳሪ ሀገርና ወጣት ለመፍጠር ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- በሪፎርም ሥራችን ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት እያደረግን ያለነው በዘርፉ ተወዳዳሪ ሀገር እና ወጣት ለመፍጠር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተገኙበት 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከአምሥቱ ብዝኃ ዘርፎች (የዕድገት ምሰሶዎች) አንደኛው ቴክኖሎጂ የሆነበት ምክንያት ነገ ለትውልድ ካለው ፋይዳ አንጻር መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ አንጻር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በማሳያነት ጠቅሰው፤ የዛሬ ሥድስት ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ስታቋቁም አንድም የአፍሪካ ሀገር በተቋም ደረጃ ኤ አይ አለመፍጠሩን አንስተዋል።

በሌላው ዓለምም ቢሆን በግሉ ዘርፍ ከሚነገረው ውጭ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ አሁን በሚታየው ልክ የመንግሥታት ዋነኛ አጀንዳ እንዳልነበረ ጠቁመዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ሲገነባ የነበረው የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው፤ ቢበዛ እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ሥራ እንደሚጀምር አመላክተዋል።

ይህ የኤ አይ ዩኒቨርሲቲም ከዓለም ሁለተኛው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ይህ ሁሉ ዝግጅት የሚደረገው አባቶቻችን የኢትዮጵያ አየር መንገድን በጊዜው መሥርተው ዛሬ ከአፍሪካ አንደኛ እንደሆነው፤ የኢትዮጵያን አየር ኃይልንም በጊዜው መሥርተው ዛሬ በአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል ከሚባሉት አንዱ እንደሆነው ሁሉ፤ ነገም የእኛ የኤ አይ ዩኒቨርሲቲ እና ተቋም በአፍሪካ ውስጥ ስመጥር መሆን እንዲችል፣ የተስተካከለ መሠረት ይዞ እንዲነሳ በሪፎርም ውስጥ አንደኛ ቁልፍ ጉዳይ አድርገን ስንሠራ ቆይተናል ሲሉ አብራርተዋል።

ሥራው ብዙ ውጤት እንደተገኘበት በመግለጽ፤ ከዚህ በላይ ደግሞ ለልጆቻችን ውጤታማ ዘመን እንፈጥርላቸዋልን ብለዋል።

ከዛሬ 10 ዓመት ገደማ ጀምሮ ዓለም ለሥራ ከሚፈልጋቸው ሰዎች መካከል ከሞላ ጎደል 50 በመቶው የሚገኘው አፍሪካ ውስጥ እንደሚሆንም አመላክተዋል።

ይህንን ዕንቁ ዕድል በወጉ ተረድቶ ወጣቱን ለነገ ውድድር ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም በአጽንኦት ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር የእኛ ሪፎርም ምን ያህል ትውልድ ላይ አበክሮ እንደሠራ ለማየት አንደኛው መገለጫ ቴክኖሎጂ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም