መምህራን ለትውልድ ግንባታ ያላቸው አበርክቶ በመንግስትና በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
መምህራን ለትውልድ ግንባታ ያላቸው አበርክቶ በመንግስትና በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- መምህራን ለሀገርና ለትውልድ ግንባታ ያላቸው አበርክቶ በመንግስትና በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጠው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ የሚገኙ መምህራን የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን የመምህራን የመኖሪያ መንደር ግንባታ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።
በዚህም በ57 ማኅበራት የተደራጁ 6 ሺህ 194 መምህራንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ተጠቃሚዎቹ የቤቱን ጠቅላላ ዋጋ 25 በመቶ አስቀድመው የቆጠቡ ናቸው።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ፈጣን ለውጥ በማስመዝገብ ለመኖር ምቹ እና ለጎብኚዎች ሳቢ እየሆነች መጥታለች።
ይህንን ዕድገት ተከትሎ የሚመጣውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ አማራጮች የቤት ግንባታዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ተችሏል ያሉት ከንቲባዋ፤ ዛሬ ደግሞ የሀገር ግንባታ ምሰሶ ለሆኑት መምህራን ልዩ ትኩረት በመስጠት ይህን ግንባታ ጀምረናል ብለዋል።
በማህበር ቤት ግንባታ መምህራን ፋና ወጊዎች ናቸው ያሉት ከንቲባዋ መምህራኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በመቆጠብ አስደናቂ ውጤት አስመዝግበዋል ነው ያሉት።
አስተዳደሩ ለመጀመሪያው ዙር የሚውል 40 ሄክታር መሬት ለመምህራኑ ያዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው መምህራን ሀገርን ለመገንባት ለሚከፍሉት ዋጋ በመንግስትና በህዝብ ዘንድ ያለውን ክብር በተግባር ያሳየንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ትምሀርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዛሬው ዕለት በ57 ማህበራት የተደራጁ 6ሺህ 194 መምህራን የግንባታ መርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ መምህራን የትውልድ ቀራጭ፣ የሀገር ግንባታና የብልፅግና መሰረት በመሆናቸው ለሙያው የሚገባውን ክብር ለመስጠት ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የመምህራንን የቤት ችግር በዘላቂነት መፍታት ሙሉ ትኩረታቸውን በትምህርት ጥራትና በትውልድ ግንባታ ላይ እንዲያደርጉ ማስቻል ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ ቤቶቹ በጣም ባጠረ ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለተጠቃሚዎች እንዲቀርቡ ለማድረግ የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ፤ አስተዳደሩ ለመምህራን ትኩረት በመስጠት የቤት ጥያቄያቸውን የሚመልሥ ተጨባጭ ተግባር እያከናወነ በመሆኑ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ይህ ምላሽ በመምህራን ዘንድ ለዓመታት የቆየውን የኑሮ ጫና የሚቀንስና በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የተሻለ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ መምህር እንዳልካቸው ደጀኔ፣ መምህር መስከረም ጎቤና እና መምህር ደለለኝ አስማሬ መምህራኑ ለረጅም ጊዜ ሲያቀርቡት የነበረው የቤት ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአስተዳደሩ ምላሽ በማግኘቱ አመስግነዋል።