ቀጥታ፡

የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 97 ሚሊዮን ደርሷል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 97 ሚሊዮን መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ተገኝተው በመንግሥት የ6 ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዲጂታል ዘርፉ በተለይም የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።

ለውጡ ሲመጣ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 37 ሚሊዮን እንደነበር በመጥቀስ፥ አሁን ላይ በኢትዮ ቴሌኮም  87 ሚሊዮን በሳፋሪ ኮም ከ10 ሚሊዮን በላይ በድምሩ 97 ሚሊዮን የሞባይል ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም ከለውጡ ወዲህ በ60 ሚሊዮን መጨመሩን ያሳያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሆኖም ይህ በቂ እንዳልሆነና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሞባይል ተጠቃሚ እንዲሆን መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የ4 ጂ እና 5 ጂ ኔትወርክ አገልግሎት ተደራሽነት እየተስፋፋ መሆኑን አንስተው፥ 1 ሺህ 70 ከተሞች የ4 ጂ እንዲሁም 28 ከተሞች የ5 ጂ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም ዜጎች የተሳለጠ ንግድና አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ ነው ብለዋል።

በፋይናንስ ዘርፉ ከሦስት ዓመታት ወዲህ በሞባይል የገንዘብ ዝውውር የሚፈጽሙ ዜጎች ቁጥር 58 ሚሊዮን መድረሱን ጠቅሰዋል።

የዲጂታል ግብይት ስርዓቱም በጥሬ ገንዘብ ከሚደረግ ግብይት መብለጡን ጠቅሰው፥ ይህ የኢትዮጵያ የዝላይ ጉዞ የፖሊሲ ውጤት ስለመሆኑ አንስተዋል።

በዲጂታል ክፍያ አገልግሎትም ባለፉት ስድስት ወራት የተመዘገበው ውጤት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር በ60 በመቶ መጨመሩን ጠቅሰዋል። 

የዲጂታል ገንዘብ ቁጠባና ብድር አገልግሎትም ማደጉን ነው ያስረዱት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም