በኮምቦልቻ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በኮምቦልቻ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ኮምቦልቻ፤ ጥር 27/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
በኮምቦልቻ ከተማ ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነቡ ካሉ የልማት ፕሮጀክቶች ሶስቱ ተጠናቀው ለምረቃ በቅተዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወንድወሰን ልሳነወርቅ በወቅቱ እንደገለጹት፣ በከተማዋ ዘላቂ ሰላምን ከማምጣት ጎን ለጎን ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው።
በበጀት ዓመቱ በአቅመ ደካማ ዜጎች ቤት ግንባታ፣ በተማሪዎች ምገባ፣ የመስሪያና መሸጫ ሼዶች ግንባታን ጨምሮ ገበያን በማረጋጋት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በከተማዋ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል ።
በከተማ አስተዳደሩ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሳይ አየለ በበኩላቸው፣ በከተማዋ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የመንገድ፣ የትምህርት ቤት፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።
ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነቡ ካሉ የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ የሰባት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ፣ 45 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥና ሁለት ኪሎ ሜትር የኮብል ስቶን መንገድ ይገኝበታል ብለዋል።
ዛሬ ግንባታቸው ተጠናቆ ለምረቃ የበቁት የወጣቶች መዝናኛ ሥፍራዎች፣ የመስሪያና የመሸጫ ሼዶች እንዲሁም የትምህርት ቤት መጸዳጃ ቤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
አስተያየት ከሰጡት መካከል መሀመድ ሲራጅ እና አምሳለ ሀብታሙ የልማት ፕሮጀክቶቹ ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል።
በከተማዋ የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች በወቅቱ ተጠናቀው ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።