አስተዳደሩ የመዲናዋን የቤት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ልዩ ልዩ የቤት ግንባታ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
አስተዳደሩ የመዲናዋን የቤት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ልዩ ልዩ የቤት ግንባታ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤት አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ልዩ ልዩ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ የሚገኙ መምህራን የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን የመምህራን የመኖሪያ መንደር ግንባታ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል።
በዚህም በ57 ማኅበራት የተደራጁ 6ሺህ 194 መምህራንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ተጠቃሚዎቹ የቤቱን ጠቅላላ ዋጋ 25 በመቶ አስቀድመው የቆጠቡ ናቸው።
ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ፈጣን ለውጥ በማስመዝገብ ለመኖር ምቹ እና ለጎብኚዎች ሳቢ እየሆነች መጥታለች።
ይህንን ዕድገት ተከትሎ የሚመጣውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ አማራጮች የቤት ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ተችሏል ያሉት ከንቲባዋ፤ ዛሬ ደግሞ የሀገር ግንባታ ምሰሶ ለሆኑት መምህራን ልዩ ትኩረት በመስጠት ይህን ግንባታ ጀምረናል ነው ያሉት።
መምህራን በማኅበር ተደራጅተውና ተገቢውን ቁጠባ በማድረግ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
አስተዳደሩ ለግንባታው የሚውል ከሊዝ ነፃ 40 ሄክታር መሬት ማዘጋጀቱን ገልጸው፤ ግንባታው በአጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ ይደረጋል ብለዋል።
መምህራን ሀገርን በመገንባትና ትውልድን በመቅረጽ በኩል እያበረከቱት ያለውን የማይተካ ሚና አድንቀው፤ ይህ የመኖሪያ መንደር ግንባታ ሲጠናቀቅ የመምህራንን የኑሮ ጫና ከመቀነስ ባለፈ፤ በትምህርት ጥራት ማስጠበቅ ላይ የሚኖራቸውን ተነሳሽነት ያሳድጋል ነው ያሉት።