የማኅበራዊ ሚዲያዎችን አጠቃቀም በአግባቡ ማድረግ እንደሚገባ ምሁራን አስገነዘቡ - ኢዜአ አማርኛ
የማኅበራዊ ሚዲያዎችን አጠቃቀም በአግባቡ ማድረግ እንደሚገባ ምሁራን አስገነዘቡ
ሐዋሳ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለሀገር ዕድገትና ለገጽታ ግንባታ ማዋል በአግባቡ መምራት እንደሚገባ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት ምሁራን አስገነዘቡ።
ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ መምራት ለሰላም፣ ለሀገር ዕድገትና ገጽታ ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት መምህር መሳይ ቦጋለ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋትና እንደሀገር የተያዙ ዕቅዶችን ማሳካት የሚያስችል ዕድል እንዳለው አመላክተዋል።
ሌላው የትምህርት ክፍሉ መምህር እያዩ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ መረጃዎች ያልተገባ መልክ እንዳይኖራቸው መንግሥት የዲጂታል ሚዲያ አጠቃቀም ግንዛቤን ለዜጎች ማድረስ ላይ በይበልጥ እንዲሠራ መክረዋል።
መንግሥት የጀመራቸው የኢትዮ-ኮደርስና የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂዎች ዘመኑን የዋጁ አሠራሮችን ለመዘርጋትና ለመተግበር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩም አመላክተዋል።
የዲጂታል ዓለሙን ዕድሎች በመጠቀም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማዕከል ያደረጉ ተግባራት ላይ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ይበልጥ እንዲሠሩ ማበረታታት እንደሚገባም ነው ምሁራኑ ያስገነዘቡት።