የሸበሌ ሪዞርት ለክልሉ ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ለዘርፉ መነቃቃት ጉልህ ሚና ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሸበሌ ሪዞርት ለክልሉ ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ለዘርፉ መነቃቃት ጉልህ ሚና ይጫወታል
ጅግጅጋ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦የሸበሌ ሪዞርት ለሶማሌ ክልል ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ለዘርፉ መነቃቃት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት የክልሉ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ እምቅ የቱሪዝም ሀብት ባለቤት ብትሆንም ሀብቱን አውቆ፣ ለይቶና አልምቶ የገቢ ምንጭ ከማድረግ አኳያ ውስንነቶች እንደነበሩ ይታወሳል።
የመደመር መንግስት ቱሪዝም ለሀገር ምጣኔ-ሀብት ዕድገትና ለገጽታ ግንባታ ያለውን ፋይዳ በመረዳት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እያከናወናቸው ባሉ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገብ ጀምሯል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመሩት የገበታ ፕሮጀክቶችም አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማልማት ባለፈ ነባሮቹ እንዲታደሱና ለአካባቢው ተጨማሪ የገቢ አቅም እንዲሆኑ እያደረገ ነው።
ከገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መካከል ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣በጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማርጌሌ እንዲሁም በሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐመድ በይፋ የተመረቀው የሸበሌ ሪዞርት አንዱ ነው።
በ385 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ሪዞርት በአንድ ጊዜ 400 እንግዶችን ማስተናገድ የሚችሉ ሦስት ምግብ ቤቶች፣ ልዩ የባሕል ማዕከል፣ ዘመናዊ የክብረ-በዓላትና የስብሰባ አዳራሾች፣ የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎችና 15 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው የእግረኛ መንገዶችን ይዟል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅግጅጋ ነዋሪዎች ሪዞርቱ ለክልሉ ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ለዘርፉ መነቃቃት ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ሪዞርቱ የሶማሌ ማህበረሰብን ባህላዊ አኗኗር በሚገልጽ መልኩ መገንባቱ ለአካባቢው ልዩ ገጽታን ከማላበስ ባለፈ የክልሉን የአኗኗር ዘይቤ በቀላሉ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ነው ብለዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አብዱረህማን ኑህ ፤የሸበሌ ሪዞርት ለአካባቢው ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ለዘርፉ መነቃቃት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
መንግስት ለቱሪዝም መዳረሻ ልማት በሰጠው ትኩረት በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎች እንዲወጡና ለዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሸበሌን የመሳሰሉ ዘመናዊ ሪዞርቶች ግንባታ የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ወሳኝ መሆናቸውን በማንሳት።
ሪዞርቱ የክልሉን ባህልና አኗኗርን ከማስተዋወቅ ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተናገሩት ደግሞ በሺር መሀመድ ናቸው።
የአካባቢዉ ነዋሪዎቸ በክልሉ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶችንና የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን በመጠበቅና በመንከባከብ ሃላፊነቱን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
የሸበሌ ሪዞርት 51 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪስት አገልግሎት ይሰጣል።