ቀጥታ፡

የቦረና ላሞችን ከተሻሻሉ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል የተሻለ የወተት ምርት የሚያስገኝ ውጤት ተገኝቷል

አዳማ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፡- የኦሮሚያ ግብርና ምርምር እንስቲትዩት የቦረና ላሞችን ከተሻሻሉ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል የተሻለ የወተት ምርት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችል  ውጤት ማግኘቱን ገለፀ።


 

በአዳሚ ቱሉ ግብርና ምርምር ማዕከል የቦረና ላሞችን የውጭ ዝርያ ካላቸው ኮርማዎች ጋር በማዳቀል የተሻለ የወተት ምርት የሚሰጡ ጊደሮች እንዲወለዱ ማድረግ መቻሉን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ተሾመ ቦጋለ ለኢዜአ አረጋግጠዋል።

ከቦረና ላሞች ጋር ተዳቅለው የተወለዱ ጥጆች አስተዳደጋቸው ፈጣን ከመሆኑ ባለፈ የተሻለ የወተት ምርት የሚሰጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ጥጆቹ በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ እንደሚላመዱና በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥም መልሶ መውለድ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የቦረና ላሞች በቀን የሚሰጡት የወተት ምርት ከ2 ሊትር እንደማይበልጥ አውስተው፤ በምርምር ማዕከሉ በማዳቀል የተወለዱ ጊደሮች ግን በቀን አስከ 10 ሊተር የወተት ምርት እንደሚሰጡ አስገንዝበዋል።


 

ዝርያቸው የተሻሻሉ 120 የመጀመሪያ ትውልድ የቦረና ጊደሮችን በስድስት ወራት ውስጥ ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ መደረጉንም አስታውቀዋል።

በሁለተኛው ትውልድ በምርምር የተሻሻሉ ዝርያዎች ደግሞ በቀን ከ15 እስከ 20 ሊትር የወተት ምርት እንደሚሰጡ አመላክተዋል።

በዚህም የወተት ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደተቻለ አስረድተዋል።

በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ የደስታ አቢጃታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አማን ገመዳ፤ በምርምር ማዕከሉ ዝርያቸው ከተሻሻሉትና ከተዳቀሉት የቦረና ጊደሮች የተሻለ ምርት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ዋሪዬ ደስታ እንደገለጹት፤ የተሻለ የወተት ምርት የሚሰጡ ጊደሮች በማግኘታቸው ያሏቸውን ከብቶች የተሻለ ምርት ወደ ሚሰጡት ዝርያዎች በመቀየር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም