የንባብ ባህል እንዲዳብር በትኩረት ሊሰራ ይገባል-ደራሲያን እና ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የንባብ ባህል እንዲዳብር በትኩረት ሊሰራ ይገባል-ደራሲያን እና ምሁራን
ሮቤ ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦በህብረተሰቡ ዘንድ የንባብ ባህል እንዲዳብር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ደራሲያንና ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት አገልግሎት ከኦሮሞ ባህል ማዕከልና ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የንባብ ሳምንት ''የዳበረ የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት'' በሚል መሪ ሀሳብ በባሌ ሮቤ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የንባብ ባህልን ማጎልበት በሚቻልበትና በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በማስመልከት ኢዜአ ከደራሲያን፣ የዘርፉ ምሁራንና አንባቢያን ጋር ቆይታ አድርጓል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ኢኒስቲትዩት የሀገር በቀል ዕውቀት ዘርፍ አስተባባሪ ኑረዲን አማን (ዶ/ር)፤ የንባብ ሳምንቱ በተለይ ከመሐል አገር ርቀው የሚገኙ አካባቢዎች የሚገኙ አንባቢያን የሚፈልጉትን መጽሐፍ በቅርበት እንዲያገኙ ዕድል እንደሚፈጥር አመላክተዋል።
የንባብ ሳምንቱን ምክንያት በማድረግ ለትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት የሚደረጉ የመጽሐፍት ድጋፍ የሚታየውን የመጽሐፍት ውስንነት በመቅረፍ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
እንዲሁም በትምህርት ቤቶችና በወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት የተደራጁ ቤተመጽሐፍትን ተደራሽ ለማድረግ እና የአንባቢያንን ቁጥር ለማሳደግ ስለሚያግዝ መንግሥት በትኩረት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
ወቅቱ የዲጂታል ዘመን ነው ያሉት አስተባባሪው የንባብ ባህላችንንም ከጊዜው ጋር በበለጠ በማዘመን የሚደራጁ ቤተ-መጽሐፍት ዲጂታል አማራጮችን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባቸውም አክለዋል።
የበርካታ የአፋን ኦሮሞ ልብ ወለድ መጽሐፍት አርታኢ አቶ ኢሳያስ ሆርዶፋ በበኩላቸው፤ ንባብ ለሀገር ዕድገት ትልቅ መሰረት በመሆኑ ከቤተሰብ ጀምሮ የንባብ ባህል እንዲያድግ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ መንግስት እንደሌሎች ዘርፎች ሁሉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።
የንባብ ባህል መዳበር በምክንያት የሚያምን ትወልድ ለማፍራት ወሳኝ በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመረውን ቅንጅት ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚዘጋጁ የንባብ ሳምንት መርሃ ግብሮች የንባብ ባህልን ከማጎልበት ባሻገር የማህበረሰብ ግንዛቤን እንደሚያሳድጉም አክለዋል።
በተለይ ወጣቱን ከአልባሌ ቦታዎች ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተመጽሐፍት አገልግሎት በተለያዩ ቦታዎች የንባብ ባህልን ለማሳደግ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ከንባብ ሳምንቱ ተሳታፊዎች መካከል የሪፍት ቫሊ ኮሌጅ የሮቤ ካምፓስ ተማሪ ብላድን አህመድ ፤ ዝግጅቱ የሚፈልገውን መጽሐፍ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸመት እንዳገዘው ተናግሯል።
በዝግጅቱ ላይ የንባብ ባህልን ማጎልበት ያለውን ፋይዳ ከመረዳቱ ባለፈ ከታዋቂ ደራሲያን የህይወት ተሞክሮ ብዙ ልምድ መቅሰሙን የተናገረው ደግሞ የዋቆ ጉቱ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አወል በድሪ ነው።
የንባብ ሳምንት መርሃ ግብሩ ንባብን የማጎልበት ዓላማ ያደረጉ ጥናታዊ ጽሁፎች፣ የንባብ ምሽት፣ የመጽሐፍ ሽያጭና የባህል ፌስቲቫልን ያካተተ ነው።