ቀጥታ፡

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወጣቶች ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ እያገዘ ነው 

ቦንጋ ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማወቅ  በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል አስችሎናል ሲሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቦንጋ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።

የካፋ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢኖቬሽን መምሪያ በበጀት ዓመቱ ከ17 ሺህ በላይ ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለመስጠት ማቀዱንም ገልጿል።

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከወሰዱ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወጣት መሠረት ገብረማርያም፤ መንግስት ያመቻቸውን ዕድል በመጠቀም በሁሉም  ፕሮግራሞች  ስልጠና በማጠናቀቅ ተጠቃሚ መሆኑን ይናገራል።


 

ስልጠናው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ እውቀት ለመጨበጥና አቅሙን በማሳደግ በተሰማራበት መስክ የላቁ ተግባራትን ለማከናወን እንዳስቻለው ነው የገለፀው። 

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እንደሀገር ትልቅ እድል ይዞ የመጣ እና በተለይ ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር አብረን እንድንራመድ ያደረገ ነው ያለው ደግሞ ሰልጣኝ ወጣት ድጋፌ ደምሴ ነው፣።

በአራቱም ዘርፎች ስልጠናውን በመውሰድና የምስክር ወረቀት በመያዝ የሀገር ውስጥና የውጭ የኦንላይን የስራ እድሎችን አግኝቶ ተጠቃሚ መሆኑንም ነው የሚናገረው።


 

ስልጠናውን ዲጂታል ኢትዮጵያን ተግባራዊ ለማድረግ ለተያዘው እቅድ ስኬት የሰለጠነ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም አቅሙ የጎለበተ ዜጋን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም ነው ያመለከተው። 

የካፋ ዞን ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው፤ በዞኑ በ2018 በጀት ዓመት ለ17 ሺህ 200 ዜጎች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

ለዚህም ከመንግስትና ከግል የትምህርት ተቋማት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከሚገኙ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን /ICT/ መምህራን ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ባለፉት ስድስት ወራትም አምስት ሺህ ዜጎች ስልጠና ወስደው ሰርተፊኬት መያዛቸውን አመልክተው በቀሪ ጊዜያትም ዕቅዱን ለማሳካት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም