ቀጥታ፡

ዩኒቨርስቲው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን እውን ማድረግ የሚያስችሉ አዳዲስ የትምህርት መስኮችን ከፍቶ ሊያሰለጥን ነው

ጎንደር ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦የጎንደር ዩኒቨርስቲ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራትና ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን እውን ማድረግ የሚያስችሉ አዳዲስ የትምህርት መስኮችን ከፍቶ ሊያሰለጥን መሆኑን አስታወቀ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣የትምህርት መስኮቹ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን እውን ማድረግ የሚችል የሰው ሃይል ለማፍራት ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል።

ዲጂታል ቴክኖሎጂ የዜጎችን ኑሮ ከማቃለል ባለፈ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የሚጫወተውን ሚና ግምት ውስጥ በማስገባት ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ኢትዮጵያ አሳካዋለሁ ብላ የያዘቻቸው እቅዶች እውን እንዲሆኑ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮ መሆኑንም አብራርተዋል።

በዚህ ረገድ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮሩ አራት አዳዲስ የትምህርት መስኮችን ከፍቶ በሁለተኛ ዲግሪ ለማሰልጠን ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በትምህርት መስኮቹ ላይ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት መካሄዱን አስታውሰው፣ የሥርዓተ ትምህርት ቀረጻና ግምገማ መካሄዱንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርስቲው በተያዘው የትምህርት ዘመን ሁለተኛ መንፈቀ-ዓመት በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI)፣ በኮምፒውተር ኔት-ዎርክና ሴኩሪቲ፤ በዲጂታል ማርኬቲንግና ዲጂታል አናሊሲስ እንዲሁም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች  ተማሪዎችን ማሰልጠን እንደሚጀምር አመልክተዋል።

የትምህርት መስኮቹ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሃይል በማፍራት ኢትዮጵያ ለጀመረችው ዲጂታል ጉዞ ውጤታማነት የጎላ ሚና እንደሚኖራቸውም አብራርተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርስቲ በመደበኛና በማታ የትምህርት መርሃ-ግብሮች ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች እያሰለጠነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም