ቀጥታ፡

መንግሥት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና አሳታፊ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦ መንግሥት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና አሳታፊ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን አሳይቷል ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግሥትን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም የዘንድሮው ምርጫ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊ፣ አካታች እና ካለፈው ምርጫ የተሻለ እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

መንግሥት የምርጫ አውዱን ለማስፋት በተለየ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመው በዚህም አሁን ካለው እስከ 10 እጥፍ የሚሆኑ ልዩ ድምፆች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይገኛሉ ሲሉም ገልጸዋል።

የዘንድሮውን ምርጫ ተዓማኒ ካለፈው የተሻለ አሳታፊ እና አካታች ለማድረግ ምቹ ከባቢ መፍጠር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) መንግሥት ከምርጫው ዝግጅትና ዲሞክራሲያዊነት አንፃር ለቀረበለት ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል፡፡

መንግሥት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ እና አሳታፊ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መስፍን እርካቤ፤ ምርጫውን ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማከናወን የሚያስችል አውድ መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሕልውና ዘመቻ ላይ በነበረችበት ወቅትም ምርጫ ማካሄዷን አስታውሰው፤ የዘንድሮውን ምርጫ ሊያስተጓጉል የሚችል የሰላም እጦት የለም ነው ያሉት፡፡

ምርጫው ፍትሐዊ ዲሞክራሲያዊና በሕዝቡ ዘንድ ተዓማኒ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸው፤ ለዚህም ፓርቲዎች የእጩዎች ምዝገባ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካሪ ምክር ቤት አባል ዑስታዝ ካሚል ሸምሱ፤ ምርጫ የአንድ ማኅበረሰብ የዲሞክራሲ ልምምድ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ባሻገር ደግሞ ማኅበረሰቡ ምርጫው አሳታፊ እንዲሆን ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

#Ethiopian_News_Agency

#ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም