የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ ተግባራዊ ሊያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ ተግባራዊ ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልገሎት መስጠት የሚያስችል የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ ማድረጉን አስታወቀ።
የሰሌዳ ለውጡ ከነገ ጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የሎጂስቲክስ ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር እሸቱ ፊጣ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጡን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጡ ተቋሙ እያከናወነ ያለው ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ሥራ አካል ሲሆን ተሽከርካሪዎቹ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር እንዲኖራቸው ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል አገልግሎት ላይ የቆየው ሰሌዳ ወጥነት የሌለው እና የተዘበራረቀ በመሆኑ ለአሠራር አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
ተቋሙ ዘመኑን የሚመጥን ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለውጥ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የሰሌዳ ለውጡ ለዜጎች የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣን፣ ዘመናዊና ግልጽ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የተቋሙን ተሽከርካሪ በመጠቀም የሚፈጸም የስነ-ምግባርና መሰል ጥሰቶችን በተሟላ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር አረጋግጠዋል።
ከነገ ጀምሮ በይፋ ተግባራዊ የሚደረገው ይህ አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ከዲጂታል የመረጃ ቋት ጋር የተሳሰረ መሆኑ ለአሠራርና ለቁጥጥር መጠናከር እንዲሁም ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
አዳዲሶቹ ሰሌዳዎች በህገ-ወጥ መንገድ የማይባዙና የደህንነት መጠበቂያ ሚስጥራዊ መለያ ያላቸው በመሆናቸው ለየትኛውም የማጭበርበር ወንጀል ተጋላጭ እንደማይሆኑ ገልጸዋል።
ይህም የተቋሙን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚጨምርና አገልግሎቱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ስለመሆኑ በማብራሪያቸው አንስተዋል።