ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን አዎንታዊ ሚና ለመወጣት ተዘጋጅተናል - የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን አዎንታዊ ሚና ለመወጣት ተዘጋጅተናል - የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018(ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን አዎንታዊ ሚና ለመወጣት ሰፊ ዝግጅት ማድረጉን የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አስታወቀ።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በቀጣይ የሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ እንዲሆን ምክር ቤቱ ሰፊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የምርጫ ትምህርትና ግንዛቤ፣ የፓርቲዎች ክርክርና የግልጽነት መድረኮች ማመቻቸት እንዲሁም የምርጫ ታዛቢነት ሥራቸውን ለመወጣት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከ200 በላይ የሲቪክ ማኅበራት በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ፈቃድ መውሰዳቸውን ጠቁመው፤ ተቋማቱ ወደ ሥራ መግባት የሚያስችላቸውን ምስክር ወረቀት ከምርጫ ቦርድ እንዳገኙ በይፋ ተግባራቸውን ይጀምራሉ ብለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ አዲስ አዋጅ መውጣቱንና ምቹ አሠራሮች መዘርጋታቸውን አስታውሰው፤ ይህም የሲቪክ ማኅበራት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደጉን ፕሬዝዳንቱ አውስተዋል።
ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሀገርን ለማሻገር፣ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍና ስልጡን የፖለቲካ ባህልን ለማሳደግ ወሳኝ መሣሪያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው ይጠቅመኛል የሚሉትን መንግሥት በሰላማዊ መንገድ በድምፃቸው እንዲመርጡ ሰፊ የምርጫ ትምህርት ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳባቸውን ለሕዝብ የሚያስተዋውቁበት መድረክ በማመቻቸት፣ መራጮች የሚበጃቸውን አካል በዕውቀት ላይ ተመስርተው እንዲመርጡ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።
በሌላ መልኩ የምርጫውን ሂደት ታማኝነት ለማረጋገጥ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ በታዛቢነት በመሳተፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ጠቅሰዋል፡፡