የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ይጀመራል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሲዳማ ቡና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 18 ጨዋታዎች በስድስቱ አሸንፎ በአራቱ ተሸንፎ ስምንት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
11 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያሳርፍ 10 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ26 ነጥብ 7ኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና 18 ጨዋታዎችን አከናውኑ ዘጠኝ ጊዜ ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል።
በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 24 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ሲዳማ ቡና በ34 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አላሸነፈም። ሲዳማ ቡና ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል አልቀናውም።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ። ሲዳማ ቡና ካሸነፈ በሊጉ የመጀመሪያ ዙር መሪ ሆኖ ያጠናቅቃል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር አዳማ ከተማ ከሃዋሳ ከተማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዳማ ከተማ በውድድር ዓመቱ 18 ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። 10 ጊዜ አቻ ወጥቷል።
15 ግቦችን በ18ቱ ጨዋታዎች ላይ 15 ግቦችን ሲያስቆጥር 12 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ28 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሊጉ ካከናወናቸው 18 ጨዋታዎች መካከል ዘጠኙን ያሸነፈው ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ አራት ጊዜ ተሸንፏል። አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 20 ግቦችን ሲያገባ 10 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ሃዋሳ ከተማ በ32 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው አዳማ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። ሃዋሳ ከተማ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከመቻል ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሀዲያ ሆሳዕና በ20 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል። መቻል በ29 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ባለፉት ሁለት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች የተሸነፈው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
በ18ኛ ሳምንት በሸገር ከተማ 1 ለ 0 የተሸነፈው መቻል ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ የሚደረገው ጨዋታ ሸገር ከተማ እና ምድረ ገነት ሽሬን ያገናኛል።
ሸገር ከተማ በ20 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። ምድረ ገነት ሽሬ በ22 ነጥብ 11ኛ ላይ ተቀምጧል።
በ18ኛ ሳምንት መቻል ያሸነፈው ሸገር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ምድረ ገነት ሽሬ ማሸነፍ የመጀመሪያውን በደረጃ ሰንጠረዥ ከወገብ በላይ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ሊያደርገው ይችላል።
የ19ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ ጥር 29 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በተመሳሳይ ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ነው።