አርሰናል በካራባኦ ዋንጫ ለፍጻሜ አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል በካራባኦ ዋንጫ ለፍጻሜ አለፈ
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2018 (ኢዜአ)፦ በካራባኦ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ አርሰናል ቼልሲን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ትናንት በኤምሬትስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ካይ ሃቨርትዝ በ97ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል። ሃቨርትዝ በቀድሞ ቡድኑ ላይ ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ቼልሲ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስድም ቡድኖቹ ግልጽ የግብ እድሎችን በበቂ ሁኔታ መፍጠር አልቻሉም።
ውጤቱን ተከትሎ አርሰናል በአጠቃላይ ድምር ውጤት 4 ለ 2 በማሸነፍ ለካራባኦ ዋንጫ ፍጻሜ ያለፈ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል።
አርሰናል ከስምንት ዓመታት በኋላ ለካራቦኦ ዋንጫ ፍጻሜ ደርሷል።
መድፈኞቹ ውድድሩን ለሶስተኛ ጊዜ ለማሸነፍ ከማንችስተር ሲቲ እና ኒውካስል ዩናይትድ አሸናፊ ጋር በዌምብሌይ ስታዲየም ይጫወታሉ።
የአምስት ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ቼልሲ ከእ.አ.አ 2024 በኋላ ለፍጻሜ የማለፍ ውጥኑ ሳይሳካ ቀርቷል።
ሁለተኛው የካራባኦ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ነገ በማንችስተር ሲቲ እና ኒውካስል ዩናይትድ መካከል ይደረጋል።