የአዲስ - ሰበታ -ሆለታ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታን ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ - ሰበታ -ሆለታ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታን ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ - ሰበታ -ሆለታ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታን አጠናቆ ለመጨረስ ከተቀመጠለት የሶስት ዓመት ጊዜ ቀደም ብሎ በሁለት ዓመታት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የአዲስ አበባ- ሰበታ -ሆለታ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሂደትን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥቷል።
አስተዳደሩ ከአዲስ አበባ ወደ ወልቂጤ፣ ጅማ እና ጋምቤላ እንዲሁም ወደሌሎች አጎራባች የክልል ከተሞች ያሉ የትራፊክ እንቅስቃሴዎችን ለማቀላጠፍ የአዲስ - ሰበታ -ሆለታ የመንገድ ፕሮጀክትን ግንባታን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የማዕከላዊ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ፕሮጀክት ቡድን መሪ ኢንጅነር መኮንን መንገሻ የአዲስ - ሰበታ -ሆለታ የመንገድ ፕሮጀክት የዲዛይን ሥራዎች፣ ከወሰን ማስከበር ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን መፍትሔ በማስቀመጥ ግንባታው ተጀምሯል።
የመንገድ ግንባታው ከተጀመረ ሁለት ወራት ከ15 ቀን እንደሆነው ገልጸው ግንባታው 50 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገድ ግንባታ በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ እንደሚከናወን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በመጀመያው ምዕራፍ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት የሚስተዋልበትን የአዲስ - ሰበታ 11 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የመንገድ ግንባታ ስራ በዚህ ዓመት በፍጥነት ለመጨረስ ግብ ይዞ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
እየተሰሩ ካሉ ተግባራት መካከል የአፈር ቆረጣ፣ የማፋሰሻ ቱቦ ቀበራ፣ የድጋፍ ግንብ ግንባታ ሥራዎች እና ሌሎች ከመንገድ ሥራ ጋር የተገናኙ ተግባራት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ ፕሮጀክት የከተማ መንገድን ማለትም የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የብስክሌት መስመሮችን ባሟላ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ አክለዋል።
የመንገድ ስራው ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚካሄድ በመሆኑ በሁለተኛው እና በሶስተኛው ምዕራፍ ከሰበታ እስከ ሆለታ እና ሱባ መናፈሻ ፓርክ የመንገድ ግንባታ የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ግንባታውን በሦስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ የጊዜ ገደብ መቀመጡን በማውሳት፥ ለግንባታው ከተፈጠረው ምቹ መደላድል አንጻር ፕሮጀክቱን በሁለት ዓመት ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱ ተጠሪ ኢንጅነር መልካሙ ጋረደው በበኩላቸው፤ ከፍተኛ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የሚደረግበት ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ግንባታው እንዲከናወን ድጋፍና ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያገኘናቸው አሽከርካሪ አቶ አብዱልቃድር መሀመድ እና አቶ ሚልኬ ሱኬ በበኩላቸው የአዲስ - ሰበታ -ሆለታ የመንገድ ፕሮጀክት ከፍተኛ የትራፊክ መጨናቀቅን የሚፈታ በመሆኑ ተስፋ ጥለንበታል ብለዋል።
የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግንባታውን በፍጥነት በመጨረስ ለአገልግሎት ማብቃት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።