ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የግብርና ትራንስፎርሜሽን የሚያፋጥኑ የዲጂታል ተግባራት ተጠናክረው ቀጥለዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦ በግብርናው ዘርፍ የተጀመረውን የዲጂታላይዜሽን ስራ የበለጠ የሚያጠናክሩ ውጤታማ ትግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ በግብርናው ዘርፍ የተጀመረውን የዲጂታላይዜሽን ስራ ይበልጥ የሚያጠናክርና መረጃዎችን በአንድ ቋት የሚያገናኝ "Ethiopia OpenAgriNet" የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

ፕሮጀክቱ እስካሁን በተለያዩ ተቋማትና በተበታተነ መልኩ የሚገኙ የግብርና መረጃዎችን በአንድ የዲጂታል መረብ ውስጥ በማቀናጀት ለተጠቃሚዎች ምቹና ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።


 

በኢንስቲትዩቱ የኦፕሬሽን ሲነየር ዳይሬክተር ዳዊት ፊሊጶስ እንደገለጹት፣ አዲሱ ዲጂታል ሥርዓት አርሶ አደሮችን፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎቶችን፣ የገበያ እና የአየር ንብረት መረጃዎችን እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ የሚያስተሳስር ነው።

ይህም ወቅታዊ መረጃዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች ማግኘት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል

ስርዓቱ በተለይ በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ አወጣጥ ሂደትን ከመደገፉ ባለፈ፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን በማጠናከር ሴቶችንና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል።

መረጃን መሰረት ያደረገ የግብርና ውሳኔ አሰጣጥን ለማጎልበትና ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማገዝ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።


 

በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ኢኖቬሽን ዳይሬክተር ግሩም ከተማ(/) በበኩላቸው፣ ስርዓቱ ደህንነቱ የተጠበቀና ከሀገሪቱ የዲጂታል ስትራቴጂ ጋር በተጣጣመ መልኩ የተዘጋጀ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የግብርና ምርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ የያዘው ይህ ፕሮጀክት፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በማፋጠን ዘርፉ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ነው ብለዋል።


 

ዲጂታል ስርዓቱን በትብብር ካዘጋጁት መካከል በዱባይ የፕሮቴን ኢንተርናሽናል የቢዝነስ ባለሙያ አሺሽ ቻተርጂ በበኩላቸው ዛሬ ይፋ የሆነው ፕሮጀክት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆን ትክክለኛና ወቅታዊ የአየር ሁኔታ፣ የገበያ መረጃ እና የግብርና ምክረ-ሀሳቦችን በቴክኖሎጂ አማካኝነት በቀላሉ ማግኘት ያስችላል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እንደሚያፋጥንም  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም