ቀጥታ፡

በብሔራዊ የምግብ ስርዓት ሽግግር ፕሮግራም የተገኙ ውጤቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል

ሐዋሳ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦ በብሔራዊ የምግብ ስርዓት ሽግግር ፕሮግራም የተገኙ ውጤቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የሲዳማ ክልል የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንና ኒውትሪሽን ክልላዊ ፍኖተ ካርታ ማስተዋወቂያ መድረክ በሃዋሳ ተካሂዷል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የምግብ ስርዓት ሽግግርና ኒውትሪሽን የክልሎች አስተባባሪ አካሉ ዳፊሳ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ እንደሀገር ተግባራዊ በተደረገው የምግብ ስርዓት ሽግግር ፕሮግራም ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡


 

ፕሮግራሙ የተባበሩት መንግስታት የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳከት ቁልፍ ሚና የሚጫወት በመሆኑ እንደሀገር የምግብ ስርዓት ሽግግር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ እየተሰራበት ነው ብለዋል፡፡

በዘርፉ የተገኘውን ውጤት ቀጣይነት ለማረጋገጥም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው ሲዳማ ክልልም የፍኖተ ካርታ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

ሀገራዊ ፕሮግራሙ የምግብ ስርዓትን በማሻሻል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ደህንነቱ የተጠበቀ የተመጣጠነ ምግብ ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

በቀጣዮች ወራት የሁሉንም ክልሎች የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንና ኒውትሪሽን ፍኖተ ካርታ በማጠናቀቅ የተደመረ አቅም የመፍጠርና በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን ውጤታማነት ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሌማት ትሩፋት፣ በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በሰቆጣ ቃል ኪዳንና በሌሎች አዳዲስ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች የተገኙ ውጤቶች ለፕሮግራሙ ስኬት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪና የክልሉ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንና ኒውትሪሽን ምክር ቤት ሰብሳቢ ተወካይ ተሰማ ዲማ ፕሮግራሙን በክልል ደረጃ በ2014 ተግባራዊ በመደረጉ የመቀንጨር ምጣኔን መቀነስ እንደተቻለ ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ በ22 ወረዳዎች የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነትን መሰረት ያደረጉ ስራዎች በመስራት ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትና ነፍሰ ጡር እናቶችን አመጋገብ ስርዓት መሻሻሉን ተናግረዋል፡፡

እንደ ክልል የተዘጋጀው የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽንና ኒውትሪሽን ፍኖተ ካርታ ቅንጅታዊ ስራን በማጠናከር የተገኙ ውጤቶችን በሚያስቀጥል ሀገራዊ ግብን ማሳካት የሚያስችል አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የተዘጋጀው የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ለፕሮግራሙ ስኬት የተቋማትንና የዜጎችን ድርሻ በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም ማኔጀር ብርሃኑ ቱንሲሳ ናቸው፡፡

በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ከመሬት አጠቃቀም ጀምሮ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲመረትና የተመጣጠነ ምግብ ለማህበረሰቡ እንዲቀርብ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት ይከናወናሉ ብለዋል፡፡

በመድረኩ በፍኖተ ካርታው በተቀመጡ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም