በአስተዳደሩ የከተማ እና የገጠሩን ማህበረሰብ የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው-ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
በአስተዳደሩ የከተማ እና የገጠሩን ማህበረሰብ የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው-ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ አስተዳድር የከተማ እና የገጠሩን ማህበረሰብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
የአስተዳደሩ ምክር ቤት 3ተኛ የስራ ዘመን 5ተኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ላይም ከንቲባ ከድር ጁሃር የአስተዳደሩን የአስፈፃሚ እና የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ከንቲባ ከድር በወቅቱ እንዳሉት፤ ባለፉት ስድስት ወራት የከተማ እና የገጠሩን ማህበረሰብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት አበረታችና ውጤታማ ናቸው።
በተለይ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በስፋት በማምረትና አቅርቦትን በሰንበት ገበያዎች ተደራሽ በማድረግ ገበያን ለማረጋጋት የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አንስተዋል።
ለነዋሪው የሚሰጡ አገልግሎቶችን በዲጂታልና ከወረቀት ንኪኪ የፀዱ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት የተገልጋዩን እርካታ እያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በመሶብ ድሬ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የፌዴራልና የአስተዳደሩ ተቋማት 62 ዓይነት አገልግሎቶችን ለ9 ሺህ 760 ተገልጋዮች ተደራሽ ተደርገዋል ብለዋል።
በሌላም በኩል በገጠርና በከተማ ለሚገኙ ከ16 ሺህ 200 በላይ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን አንስተው ከነዚህም መካከል ከ11 ሺህ 600 በላይ የሚሆኑት ቋሚ የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አብዲ ሙክታር ፤በትምህርት ንቅናቄ ረገድ የተሰሩ ስራዎች፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የታዩ አበረታች ውጤቶች ይበልጥ ለማሳደግ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።
ደጋፍና ክትትሉም የአምራች ኢንዱስትሪው ተኪ ምርቶችን በስፋትና በጥራት እንዲያመርት ከማስቻል ባለፈ ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር የላቀ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በግማሽ በጀት ዓመቱ በገጠርና በከተማ የተሰሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በየደረጃው የሚገኘውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።
እነዚህን ውጤቶች በማስቀጠል በተለይ የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የተጀመሩ ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ ከንቲባ ከድር ጁሃር ባቀረቡት ሪፖርት ላይ በሰፊው ከተወያየ በኃላ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀ ሲሆን መደበኛ ጉባኤውንም በነገው ዕለት ያጠናቀቃል።