የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ የብሄራዊ ጥቅምና የጋራ አጀንዳ በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ ማግኘት አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ የብሄራዊ ጥቅምና የጋራ አጀንዳ በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ ማግኘት አለበት
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ የብሄራዊ ጥቅምና የጋራ አጀንዳ በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የቀይ ባሕርን ጉዳይ በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያለው ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ ጥረት እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ቀይ ባህር ለዘለዓለም ተነጣጥለው እንደማይኖሩ በመግለጽ ፍትሐዊ ጥያቄያችን በሰላማዊ፣ በሰጥቶ መቀበልና በድርድር መርህ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ ፍትሐዊ ካልሆነ በዓለም ላይ ፍትሕ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ መልስ ማግኘቱ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መስፍን እርካቤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ ምንም አይነት ልዩነት ሳይገድበን የጋራ አቋም ሊኖረን ይገባል ነው ያሉት፡፡
ብሔራዊ ጥቅም የህልውና ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ የባህር በር ጉዳይን በሰላማዊ መንገድ ዕልባት እንዲያገኝ ማድረግ ግዴታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ የበለጸገችና የተከበረች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የቀይ ባህር ጉዳይ በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ የጋራ መግባባት የተፈጠረበት አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የምክር ቤት አባል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ የምታነሳው ጥያቄ ፍትሕን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ከቀይ ባህር ባለቤትነት የራቀችው በወቅቱ በነበረው መንግሥት ቸልተኝነት መሆኑን በመጥቀስ፤ እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ይዛ የባህር በር ሊዘጋባት እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲና የመደራደር አቅም እያደገ መምጣቱን በመግለጽ፤ ጥያቄያችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል፡፡
ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል መብራቱ ዓለሙ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያውያን ቀይ ባህር የብሔራዊ ጥቅማችን አጀንዳ በመሆኑ በጋራ መስራት አለብን ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚያሳዩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እያደረገች መሆኑን በማንሳት፤ እኛም የፖለቲካ ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በመንግሥት በኩል እየተከናወኑ ያሉ በሳል የውጭ ግንኙነት ስራዎች ኢትዮጵያን በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተሻለ ሆና መውጣት ያስችሏታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡