ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚው ዘርፍ የተገኙ ስኬቶች በበጀት ዓመቱ የተያዘውን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ያሳዩ ናቸው - የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚው ዘርፍ የተገኙ ስኬቶች በበጀት ዓመቱ የተያዘውን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል ያሳዩ ናቸው - የምክር ቤት አባላት
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢኮኖሚ ስብራትን ለመጠገን ያለመ መሆኑን አንስተዋል።
ማሻሻያው ኢኮኖሚውን ከግብርና መር ወደ ብዝኃ ዘርፍና ብዝኃ ተዋናይ በመቀየር ጥራት ያለው እድገትን ማረጋገጥን እንዲሁም የዕዳ ጫናን የማቃለል ዓላማን የያዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻያው ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ወጣቱን ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስቸሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው ብለዋል።
በሰውሰራሽ አስተውሎት፣ በቅድመ መደበኛ የህጻናት ትምህርት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በከተማ ልማት ላይ የሚታይ ለውጥ መመዝገቡንም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በሁሉም ዘርፎች ከሚጠበቀው የላቀ አመርቂ ውጤት ማምጣት ያስቻለ ነው ብለዋል።
የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ አጋማሽ የእድገት አፈጻጸምን በመገምገም ኢትዮጵያ በዓመቱ መጨረሻ የ10 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንድታስመዘግብ የእቅድ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የምክር ቤት አባል ነጃት ግርማ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እና እያመጣ ያለው ለውጥ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በተጨባጭ የሚታይና የሚዳሰስ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ዋጋ ከፍላ ራሷን ከእዳ እያላቀቀች የመጣችበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
በብዝኃ ዘርፍ ላይ የተመሰረተው ኢኮኖሚ በሁሉም ዘርፍ ውጤት እያስመዘገበ ነው ያሉት የምክር ቤት አባሏ፥ ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚው ዘርፍ አስደናቂ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛው የምክር ቤት አባል አጉ ደባን በበኩላቸው በግማሽ ዓመቱ የተመዘገበው ውጤት በበጀት ዓመቱ የተያዘውን እቅድ ማሳካት እንደሚቻል የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም አሳይቷል ብለዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍና በሌሎችም መስኮች የተገኙ ውጤቶች ኢትዮጵያ ያለችበትን የከፍታ ጉዞ የሚያሳዩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የምክር ቤት አባል ዳውድ መሀመድ ናቸው።