በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፎካከር ዝግጅት እያደረኩ ነው - ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ - ኢዜአ አማርኛ
በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፎካከር ዝግጅት እያደረኩ ነው - ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፎካከር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አስታወቀ።
ፓርቲው ለመጪው ምርጫ የሚመራበትን ፍኖተ ካርታ የያዘ ስትራቴጂ ሰነድ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
የስትራቴጂ ሰነዱ በያዛቸው አንኳር ጉዳዮችና አተገባበር ዙሪያ የፓርቲው አመራር አባላት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀ መንበር ዶክተር አብዱልቃድር አደም እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ልምምድ እንዲዳብር ፓርቲው የበኩሉን ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው።
ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ ፓርቲው ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ቀጣይ ተግባራቱ ፓርቲው ባዘጋጀው የምርጫ ስትራቴጂ ሰነድ ውስጥ መካተቱን አስረድተዋል።
ፓርቲው የምርጫ ተሳትፎ የሥነ ምግባር መመሪያ ማዘጋጀቱን የገለጹት ሊቀ መንበሩ፤ መርህን የተከተለ የፖለቲካ ክርክር ለማድረግም ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
የፓርቲው ዕጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች በቀጣዩ ምርጫ ገንቢ ሚና መጫወት የሚያስችላቸውን ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ካሚል ሰኢድ በበኩላቸው፤ ፓርቲው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የምትሻገረው የሕዝብና የአገር ጥቅምን ማስቀደም ሲቻል ነው ያሉት ኃላፊው፤ ፓርቲው በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መንግሥትን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሀገራዊ ምክክሩ ላይም ፓርቲው የጀመረውን ተሳትፎ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ነቢሀ መሀመድ እንዳሉት፤ ፓርቲው በመጪው ምርጫ 1ሺ 500 ዕጩዎችን ለማቅረብ እየሰራ ነው።
በምርጫው ላይ ውጤታማ በሆኑ መልኩ ለመሳተፍ ዛሬ ይፋ ያደረገው ስትራቴጂ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸው፤ የፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎችና ዕጩዎች ሚናቸውን በላቀ ደረጃ እንዲወጡ በስትራቴጂው ዙሪያ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ነጋሽ በበኩላቸው፤ የምርጫ ስትራቴጂው ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች፣ መገናኛ ብዙኃን ጨምሮ ከባላድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ያመላከተ መሆኑን ጠቁመዋል።