በጎንደር ከተማ የገጠር ቀበሌዎች የስርዓተ ምግብ ሞዴል መንደሮችን በማቋቋም ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የገጠር ቀበሌዎች የስርዓተ ምግብ ሞዴል መንደሮችን በማቋቋም ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ ነው
ጎንደር፤ ጥር 25/2018 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ የገጠር ቀበሌዎች የስርዓተ ምግብ ሞዴል መንደሮችን በማቋቋም ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ኃላፊ አቶ አበራ አደባ ለኢዜአ እንደገለጹት የስርዓተ ምግብ ሞዴል መንደሮች የሚቋቋሙት በከተማ አስተዳደሩ ስር በታቀፉ 11 የገጠር ቀበሌዎች ነው፡፡
የሞዴል መንደሮቹ ዓላማ ህጻናት በምግብ እጥረት ምክንያት ለመቀንጨር እንዳይጋለጡ ለማስቻል መሆኑንም ተናግረዋል።
በ11ዱ ቀበሌዎች በእያንዳንዳቸው እስከ ሶስት የሚደርሱ እናቶችን በፕሮግራሙ በማቀፍ በጓሯቸው የአትክልት ልማትና ዶሮ በማርባት የተመጣጠነ ምግብ ልጆቻቸውን እንዲመግቡ ይደረጋል ብለዋል።
በተጨማሪም እናቶች በንጥረ ነገሮች የበለጸገ ምግብን እንዴት ማዘጋጀት እንዳለባቸውም ተሞክሮ እየወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል።
የሞዴል መንደሮችን ለመመስረትም የፕሮግራሙ ትግበራ ሂደት በተመረጡ እናቶች እየለማ የሚገኝ የጓሮ አትክልትና የተመጣጠነ ምግብ ዝግጅት ላይ የልምድ ልውውጥ መርሃ ግብሮች መካሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡
ከሞዴል እናቶች መካከል ወይዘሮ ሀብታም መሰለ እንደገለጹት በተሰጠኝ ስልጠና በመታገዝ በጓሮዬ አትክልቶችን በማልማትና የተመጣጠነ ምግብ በማዘጋጀት ልጆቼን እየመገብኩ እገኛለሁ ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ለህጻናት ቤት ያፈራውን ከመመገብ ውጪ ንጥረ ነገሩ የተመጣጠነ ምግብ እንዴት ማዘጋጀት እንደሚቻል እውቀቱ አልነበረኝም ያሉት ደግሞ የሳቢያ ሳይና ገጠር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መብራት አለማየሁ ናቸው፡፡
በፕሮግራሙ ባገኙት እውቀት በመታገዝ አሁን ላይ ለልጆቻቸው የተመጣጠነ ምግብ አዘጋጅተው በመስጠት የአካልና የአእምሮ እድገታቸው የተሟላ እንዲሆን እየተንከባከቡ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡