ቀጥታ፡

በክልሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማሳደግ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ከፍተኛ ነው

አሶሳ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጤና አገልግሎት ጥራትን ማሳደግ ላይ መንግታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ  የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተደድር ጌታሁን አብዲሳ ተናገሩ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስደተኞች እና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት ከሱዳን ተፈናቅለው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችና ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የሚውሉ አምቡላንሶችን በድጋፍ አበርክቷል፡፡


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጌታሁን አብዲሳ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ለሚገኙ ተፈናቃዮችና  ለአካባቢው ማህበረሰብ፣ ለእናቶችና ህጻናት ጤና  የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ እየተሰራ ነው።

የዛሬው ድጋፍም የአገልግሎት አድማሱን ከማስፋት ባለፈ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ለመሰጠት ያግዛል ብለዋል።


 

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት የጤና ስርዓቱን ለማሳደግ እያከናወነ ያለውን አጋርነት  በማጠናከሩ  በድጋፍ የተገኙትን አምቡላንሶች ለተገቢው የጤና አገልግሎት ብቻ ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።

ድጋፉ የሱዳን ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ያለውን የአምቡላንስ እጥረት በመቅረፍ ህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋልም ብለዋል።


 

በስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሉዓለም ደስታ በበኩላቸው፤ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተበረከቱት አምቡላንሶች በተለይም የሱዳን ስደተኞች በሚገኙባቸው የጤና ተቋማት አካባቢ የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እንደሚቀርፉ ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ በእናቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ የጤና ችግሮችን ለመቀነስና የጤና ስርዓቱን ለማገዝ ያስችላል  ያሉት አቶ ሙሉዓለም፤ ዛሬ በተሰጡት አራቱ አምቡላንሶች የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታልን ጨምሮ የኡራ፣ የሆሞሻ እና ኩርሙክ ወረዳዎች ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም