አገልግሎቱ የሕብረተሰቡን የንባብ ባህልና ዕውቀት ለማሳደግ የሚያግዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ የሕብረተሰቡን የንባብ ባህልና ዕውቀት ለማሳደግ የሚያግዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው
ሮቤ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት በተለያዩ አካባቢዎች የሕብረተሰቡን የንባብ ባህልና ዕውቀት ለማሳደግ የሚያግዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
አገልግሎቱ ከኦሮሞ ባህል ማዕከልና ከኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ያዘጋጀው የንባብ ሳምንት ''የዳበረ የንባብ ባህል ለትምህርት ጥራት'' በሚል መሪ ሐሳብ በባሌ ሮቤ መካሄድ ጀምሯል።
በዚሁ ወቅት የአገልግሎቱ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አባተ ካሳው እንዳሉት፤ አገልግሎቱ የንባብ ባህልን በማሳደግ ራሱን በዕውቀት የሚገነባ ትውልድ ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው።
የንባብ ሳምንትን ምክንያት በማድረግም ለ12 ትምህርት ቤቶችና ለባሌ ሮቤ ማረሚያ ቤት የመጻሕፍት ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።
የኦሮሞ ባህል ማዕከል ዋና ዳይሬክተር መኪያ ጀማል በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በሀገር ዕድገት ውስጥ የራሱን ዐሻራ የሚያስቀምጥ ትውልድ ለማፍራት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከመማሪያ በተጨማሪ የተደረገው የማጣቀሻ መጸሕፍት ድጋፍ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እየተደረገ ላለው ጥረት አጋዥ ነው ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቡልቶሳ ሂርኮ (ዶ/ር) ናቸው።
የተደረገው የመጻሕፍት ድጋፍ በገንዘብ የማይተመን ዕውቀት ለማግኘት ያስችላል ሲሉም ገልጸዋል።
በንባብ ሳምንት መርሐ-ግብሩ ንባብን ማጎልበት ያለውን ፋይዳ የተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።