ኢትዮጵያ እና ቀይ ባህር ለዘላለም ተነጣጥለው መኖር አይችሉም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቀይ ባህር ለዘላለም ተነጣጥለው መኖር አይችሉም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 26 /2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቀይ ባህር ለዘላለም ተነጣጥለው መኖር አይችሉም፣ ቀይ ባህር የህልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ቀንድ እንዳይቀደድ የተሰፋ እንዳይጣመር የተቀፈደደ ነው ሲሉ በቀጣናው ያለውን ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ ገልጸዋል።
የቀጣናው ማህበረሰብ በባህል፣ ታሪክ እና በቋንቋ የተሳሰረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይሁንና ቀጣናው በከፍተኛ ፉክክር እና ጣልቃ ገብነት የተከበበ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር አይገባትም ብሎ የሚያምን ሰው ተፈጥሯዊ ህግ መሳቱንም አመልክተዋል።
ቀይ ባህር እና ኢትዮጵያ ለዘላለም ተነጣጥለው መኖር እንደማይችሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ፤ በስምምነት እና በገበያ ህግ በድርድር እንፍታ የሚል ጽኑ አቋም እንዳላት አመልክተዋል።
ቀይ ባህርን ዛሬ ላይ ለመከልከል ቢሞክር አካሄዱ አግባብ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ከተፈጥሯዊ ጸጋ ማስቀረት እንደማይቻል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላም እና በድርድር ብቻ የመፍታት ጽኑ አቋም እንዳላትም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ መቼም ሊቆም እና ሊቀር የማይችል የህልውና ጉዳይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ያለንን ሀብት በጋራ በመጠቀም በጋራ እንልማ ሲሉም ለጎረቤት ሀገራት መልዕክት አስተላልፈዋል።