ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችል መደላድል መፍጠር ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፦በሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችል መደላድል መፍጠር  እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ምክክር ልብን ያሳርፋል፤ በውይይት በርካታ ስብራቶች ይጠገናሉ ብለዋል፡፡  

አሁን ያለው ትውልድ በውይይት ሀገር መሥራት እንዳለበት ተናግረው፣ ለመወያየት ዝግጁ መሆን እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

ኮሚሽኑ እስካሁን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ማወያየቱን ጠቅሰው፤ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካ እና በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ተደራሽ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ 

በዚህም በርካታ አጀንዳዎችን መሰብሰቡን ገልጸው፣ እስካሁን የአጀንዳ ማሰባሰብና ለዋናው መድረክ የሚወያዩ ሰዎችን የመለየት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልልም ከአሥር በላይ ስብሰባዎች መደረጋቸውን ጠቁመው፣ በአጠቃላይ ከ95 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውክልና ማግኘቱንም ገልጸዋል፡፡ ምክክሩን ሊያቆም የሚችል ምንም ዓይነት ነገር አለመኖሩንም አረጋግጠዋል፡፡

የምክክሩን አካታችነት አስመልክተውም፣ አልፈልግም የሚል አካል ካለ እንደማይገደድ ነው የተናገሩት፡፡  

ስለ ምክክሩ ጠቀሜታ ለሁሉም የማስገንዘብ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ብዙኃኑ የተስማሙበት ሐሳብ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በተሰበሰቡ አጀንዳዎች ላይ በሳል ውይይት በማድረግ ለልጆቻችን ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የሚያስችል መደላድል መፍጠር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ 

የኮሚሽኑ ቀጣይ ሥራ ለዋናው ጉባኤ የተመረጡ ሰዎችን አወያይቶ፣ አጀንዳውን አብላልቶ፣ ለምክር ቤቱ እና ለመንግሥት የሚሆን ድምዳሜ ማውጣት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

እስካሁን ያለው ሂደት እጅግ ተስፋ ሰጪና ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ገልጸው፤ ለአብነትም በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸው በተግባር መረጋገጡን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም