ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ፍላጎትና አረዳድ እየተሻሻለ መጥቷል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ልዩነት የማይገድበው ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ፍላጎትና አረዳድ እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግሥትን የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

ብሔራዊ ጥቅምን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ተግባቦት እየጨመረ መጥቷል።

በጫካ ሆነው ከመንግስት ጋር የታገሉ አንዳንድ አካላት ትግላቸው መልኩን ሲስት እና የባንዳ ጣልቃ ገብነት መኖሩን ሲመለከቱ የሃሳብ ለውጥ አድርገው የተመለሱ መኖራቸውን አንስተዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ባሉበት ቦታ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ሲከሰት ለመንግስት በቂ መረጃ በመስጠት በጋራ የሚሰሩ ስለመኖራቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ገልጸዋል።

በማንኛውም የልዩነት አመለካከት ውስጥ ቢሆኑም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ጉዳይ አሳልፈው የማይሰጡ አካላት እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የማይደራደሩ አካላት በሁሉም አካባቢዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን በሚመለከት ያለው አረዳድ እየተሻሻለ መምጣቱን የሚያመላክትና የሚታይ ለውጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም