የትግራይ ክልል ህዝብ በአዲስ እሳቤ በፖለቲካ አውድ ውስጥ ተዋናይ መሆን አለበት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የትግራይ ክልል ህዝብ በአዲስ እሳቤ በፖለቲካ አውድ ውስጥ ተዋናይ መሆን አለበት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፦የትግራይ ክልል ህዝብ በፖለቲካ አውድ ውስጥ ከመድረክነት ወጥቶ በአዲስ እሳቤ የፖለቲካ ተዋናይ እንዲሆን መደገፍ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በትግራይ ክልል ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ በትግራይ ክልል አሁን አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ጠቅሰዋል።
የትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት ይፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን ካለበት ውጥንቅጥና አረንቋ በመውጣት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአብሮነት መኖርና ማደግ የሚፈልግ ቀና ህዝብ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ስልጡን ፖለቲካን በቅጡ የሚገነዘብ የታገለና ያታገለ ህዝብ እስከ ዛሬ የፖለቲካ መድረክ እንጂ የፖለቲካ ተዋናይ መሆን እንዳልቻለ ተናግረዋል።
በዚህም የትግራይ ክልል ህዝብ በቀጣይነት ራሱን በአዲስ አስተሳሰብ በመቃኘት የፖለቲካ መድረክ ከመሆን ወጥቶ ወደ ተዋናይነት መሸጋገር እንደሚገባው ገልጸዋል።ለዚህም መደገፍ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በትግራይ ክልል በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉበትን ደረጃ ማሻሻል እንደተሳናቸው አስረድተዋል።
የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች የአጃቢ ተዋናይ እንጂ የመሪ ተዋናይ ሚና መጫወት አልቻሉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አጃቢ ተዋንያን በመሆን የክልሉን የፖለቲካ ዕድገት ወደሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ አይቻልም ብለዋል።
የትግራይ ህዝብ ከመድረክነት ወደ ተዋናይነት የፖለቲካ ኃይሎችም ከአጃቢነት ወደ መሪ ተዋናይነት ሲቀየሩ የሰለጠነና ፖለቲካን በቅጡ የሚገነዘበው የትግራይ ህዝብ ብዙ ጉዳዮችን መቀየር እንደማይሳነው ገልጸዋል።