የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ታጥቋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ታጥቋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተለያየ ስምና ተግባር ያላቸው ከ100 በላይ ዘመናዊ አውሮፕላኖች መታጠቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል የተቋም ግንባታ ማብራሪያቸው÷ መንግስት የኢትዮጵያን በሁሉም መስክ የማድረግ አቅሟን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የኢትዮጵያ አየር ኃይል አንድ ቢጫ ሂሊኮፕተር ብቻ እንደነበረው አስታውሰዋል።
የተቀረው ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ዛሬ ላይ የተለያየ ስምና ተግባር ያላቸው ከ100 በላይ አውሮፕላኖችን ታጥቋል ብለዋል።
ለምንድን ነው ተቋም የሚገነባው በሚል በጠየቁት ማብራሪያቸው፤ ምሰሶ የሚገዳደሩ ኃይሎች ከመጡ ኢትዮጵያን ለማጽናትና ለማስቀጠል ነው ብለዋል።
ከጠላቶች የበለጠ ሃብት በማመንጨትና አቅም መገንባት ካልተቻለ በዲፕሎማሲና ሚዲያ ምክንያት ጫና ለመፍጠር እንደሚጥሩ አብራርተዋል።
ለምሳሌም የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያ መንግስት የውስጥ ጉዳዩን መፍታት ሳይችል ቀርቶ የቀይ ባሕር ጉዳይ ያነሳል ብለው ክስ እንደሚቀርብ አንስተዋል።
የውስጥ ጉዳያችን ላይ ሽንኩርት ከታፊው፣ በርበሬ አቅራቢው፣ አማሳዩ ተቀምጦ ሳለ ውስጥና ውጭ የሚለው ጉዳይ እንዴት ይሆናል ሲሉ ጠይቀዋል።
መፍትሔው ብቃትን በማጎልበት ጠንክሮ መገኘት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ኢትዮጵያን መጉዳት የሚፈልጉ ኃይሎች ገንዘብ ፋይናንስ ቢደረጉም ኢትዮጵያን የሚያስቆሙበት አንዳች አቅም እንደሌላቸው አረጋግጠዋል።