ቀጥታ፡

ልዩነቶችን በይቅርታ ማለፍ፣ ለውይይትና ለንግግር ሁልጊዜም ዝግጁ መሆን ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦ ልዩነቶችን በይቅርታ ማለፍ፣ ለውይይትና ለንግግር ሁልጊዜም ዝግጁ መሆን ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ።

በማብራሪያቸውም፥ ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም እጦት እንድንኖር ካደረጉን እና ካልተላቀቅንባቸው ምክንያቶች መካከል አንደኛው ከጥንት የተጣባነው ልዩነቶችን በኃይል ብቻ የመፍታት ልምምድ ነው ብለዋል።

ሁለተኛው ደግሞ አሁንም ከጥንት የመጣ የባንዳነት ልምምድ ሲሆን ሶስተኛው የጠላቶቻችን ኢትዮጵያ ካደገች የሚል ያልተቋረጠ ስጋት እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ፍላጎት የሀገሪቱን ምሰሶ ማፍረስ ሲሆን፤ የባንዳዎች ፍላጎት ደግሞ ሙሉ ቤቱን ማፍረስ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን በየዘመናቱ ብዙ ባንዳዎች ቢሞክሯትም፣ ከማቁሰል ባለፈ ሊያጠፏት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

አባቶቻችን ኢትዮጵያን ጠብቀው ለዛሬው ትውልድ ያቆዩት ከምንም ነገር በላይ የሀገርን ህልውና በማስቀደማቸው እንደሆነ ገልጸው፤ የአሁኑ ዘመን ፖለቲከኞችም ከዚህ ትልቅ ትምህርት ሊቀስሙ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመሆኑም ልዩነቶችን በይቅርታ ማለፍ፣ ለውይይትና ለንግግር ሁልጊዜም ዝግጁ መሆን ይገባል ብለዋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያን ህልውና ለማረጋገጥ በጋራ መቆም ከሁሉም ዜጋና የፖለቲካ ኃይሎች የሚጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም