ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ሀብት እና የጋራ ቁርጠኝነት የተገነባ ፕሮጀክት ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ሀብት እና በኢትዮጵያውያን የጋራ ቁርጠኝነት የተገነባ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በሰጡት ማብራሪያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ካለ አንድ ብር እርዳታ እና ብድር ያሳካ መንግስት እና ህዝብ ፕሮጀክት ሊሰራ አይችልም ማለት ተገቢ እንዳልሆነ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ አንድም ብር እርዳታ አንድም ብር ብድር እንዳልወሰደች ገልጸዋል።

ግድቡ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቁርጠኝነት እና አቋም ተገንብቶ መጠናቀቁንም አመልክተዋል።

በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነት ጨክነው በጋራ ቆመው ስለሰሩ የተከወነና የተፈጸመ ፕሮጀክት እንደሆነም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጽንኦት ያነሱት።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ በሆነው የሕዳሴ ግድብ ሳታበቃ በአፍሪካ ሶስተኛ የሆነውን የኮይሻ የኃይል ፕሮጀክት እየገነባች እንደምትገኝም ጠቁመዋል።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካን ጨምሮ በኢትዮጵያ በርካታ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን አመልክተዋል።

መንግስት ፕሮጀክቶችን የመፈጸም አቅሙ ስኬታማ እንደሆነ ገልጸው የተያዙ ፕሮጀክቶችን በጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም