የኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት አቅም 66 ነጥብ 3 በመቶ ማሳደግ ተችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት አቅም 66 ነጥብ 3 በመቶ ማሳደግ ተችሏል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራት የኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት አቅም 66 ነጥብ 3 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባ እያካሄደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዳዮች ማብራሪያቸው÷ ከሶስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ48 በመቶ ያልበለጠ ነበር ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዘርፎች የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪዎችን የምርታማነት አቅም 66 ነጥብ 3 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራትም የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች በኢነርጂ አጠቃቀም ብቻ 16 በመቶ ዕድገት ማስመዝገባቸውን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ምንጮች ለማወቅ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከግብርና ውጭ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 6 ቢዝነሶች እንዳሉ በቆጠራ መረጋገጡን አብራርተዋል።
በቆጠራ ከተለዩ የቢዝነስ ምንጮች ውስጥ 17 በመቶ ወይም 413 ሺህ የሚሆኑት አምራች ኢንዱስትሪዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ቶዮ ሶላር ኩባንያ ብቻ ባለፉት ስድስት ወራት 66 ሚሊየን ዶላር ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ወደ አምስት የሚጠጉ ሶላር ሽያጭ ላይ የሚሰሩ ፋብሪካዎች መምጣታቸውን በመጥቀስ፤ በሚቀጥለው ዓመት ሁሉም ወደስራ ይገባሉ ገሚሶቹም እየገቡ ነው ብለዋል።
በሚቀጥለው ዓመትም ከሶላር ብቻ ቢያንስ 900 ሚሊየን ዶላር ከወጪ ንግድ ገቢ ማግኘት የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመትና በተያዘው በጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ወጪ ንግድ በእጥፍ ዕድገት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተደረገው ጥረት 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ይገባ የነበረን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት እንደተቻለም አብራርተዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች በተኪ ምርት፣ በወጪ ንግድና በኢኮኖሚ ድርሻ ከፍተኛ መነቃቃትና የምርታማነት እመርታዊ አቅም መገንባቱን አስረድተዋል።
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮም ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢንዱስትሪ ዘርፍ በቢሊዮን የሚቆጠር የወጪ ንግድ ምርት ገቢ ማግኘት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
በተያዘው የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመትም መጨረሻም ከአምናው የኢንዱስትሪ ገቢ አንፃር ሲነፃጸር በእጥፍ ወደ ውጭ እንደሚላክ አስታውቀዋል።